Fana: At a Speed of Life!

ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና አዳዲስ የሚተገበሩ ህጎች

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 3 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሚደረግ ጨዋታ ይጀመራል።

ሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቫርን ጨምሮ የተለያዩ አዳዲስ ህጎችን ይተገብራል።

በዘንድሮው ውድድር በሊጉ የሚተገበሩ አዳዲስ ህጎች፤

ቅጣት ምት፦ በቅጣት ምት ወቅት ቅጣት ምት ያገኘው ቡድን ተጫዋቾች ኳሱን ለመከላከል በቆሙት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች መሃል መግባትና መቆም አይችሉም።

ቅጣት ምት ያገኘው ቡድን ተጫዋቾች ከተቃራኒዎቹ በ1 ሜትር ርቀት ካልቆሙ ቅጣት ምቱ በተቃራኒው ይሰጣል።

ግብ ጠባቂዎች ኳሱን በቀጥታ ማስጀመር አይችሉም፦ ግብ ጠባቂው ተሞክሮ የወጣ ኳስን በቀጥታ ከግብ ክልሉ ማራቅ አይፈቀድለትም።

ከዚያ ይልቅ ለተከላካይ የቡድን አጋሩ ኳሱን ግብ ክልል ውስጥ በአጭር ማቀበል ይጠበቅበታል።

ኳሱን የተቀበለው ተከላካይም ከቡድን አጋሮቹ ጋር ኳሱን መጫወት አልያም ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት ግብ ጠባቂው የሚያደርገውን ኳስን በቀጥታ ከግብ ክልል የማራቅ ሚና ይወጣል።

ተቀያሪ ተጫዋቾች፦ ተቀያሪ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ በቆሙበት ስፍራ ላይ ለመውጣት በሚቀርባቸው የሜዳው ክፍል መውጣት ይኖርባቸዋል።

ከዚህ ቀደም እንደነበረው በሜዳው አጋማሽ ክፍል መውጣትና አላስፈላጊ የጊዜ መግደያ መንገድ መጠቀም አይችሉም።

የቆሙት በማዕዘን መምቻው አካባቢም ቢሆነ በዚያው በማሳየት መውጣትና ወደ ተቀያሪዎች መቀመጫ ማምራት ግዴታቸው ይሆናል።

በሚወጡበት ጊዜም ለተመልካች ምንም አይነት አላስፈላጊ ምልክት ማሳየትም ሆነ ፍጥጫ ውስጥ መግባት አይቻልም፤ ተሰንዝሮብናል ላሉት ትንኮሳ አላስፈላጊ ምላሽ ከሰጡ የማስጠንቀቂያ ካርድ ይመለከታሉ።

የማስጠንቀቂያ ካርድ አሰጣጥ፦ በጨዋታ ወቅት ጥፋት ሲሰራና ጥፋት የተሰራበት ቡድን ጨዋታውን በቅጽበት ጀምሮ ከተጫወተ የመሃል ዳኛው ለጥፋተኛው ተጫዋች ካርድ ለማሳየት በሚል ጨዋታውን በፊሽካ ማስቆም አይችሉም።

ምናልባት በሂደቱ ለጥፋተኛው ካርድ ማሳየት ከፈለጉም የተጀመረው ኳስ ወደ ጎልነት ተቀይሮ አልያም ወደ ውጭ ወጥቶ ጨዋታውን ለመጀመር በሚኖረው ጥቂት ጊዜ ካርድ ማሳየት ይችላሉ፤ ይህም የአንደኛውን ቡድን ተጠቃሚነት (አድቫንቴጅ) ያስጠብቃል ተብሏል።

ምናልባት ግን የመሃል ዳኛው ጥፋት በተሰራበት አካባቢ በቅርበት ካሉና እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ ከከተቱ በኋላ፥ ተጫዋቾች ጨዋታውን ቢጀምሩትም ጨዋታውን በፊሽካ በማስቆም ለጥፋተኛው ካርድ ያሳያሉ።

አዲሱ ህግ የመሃል ዳኞች ሜዳ ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች ባለፈ ለአሰልጣኞችና ከሜዳው ውጭ ላሉ የቡድኑ አባላት ካርድ ማሳየት እንዲችሉም ይፈቅዳል፤ ቀይ ካርድም ሆነ ቢጫ ካርድ ማሳየትና መቅጣት።

ፍጹም ቅጣት ምት፦ የፍጹም ቅጣት ምት በሚመታበት ወቅት ደግሞ ግብ ጠባቂዎች ከግቡ መስመር ወደ ኋላ ማለፍ አይፈቀድላቸውም፤ ከዚህ ባለፈም አንድ ወይም ሁለት እግራቸው የግቡ መስመር ትይዩ ላይ መሆን ይጠበቅበታል።

በተጨማሪም ፍጹም ቅጣት ምቱ ሳይመታ የግቡን ቋሚና አግዳሚ እንዲሁም መረቡን መንካት አይፈቀድላቸውም።

የግብ ክልል ውስጥ በእጅ ከሚነካ ኳስ ጋር በተያያዘም ተጫዋቾች የሚመታን ኳስ ለማስቀረት በሚሞክሩበት ጊዜ ተፈጥሯዊ ከሆነ መንገድ ውጭ ሰውነታቸውን ማግዘፍም ሆነ እጃቸውን ማንቀሳቀስ አይችሉም።

አንድ ተጫዋች ኳስ በሚሞከርበት ጊዜ እጁን ወይም ክርኑን በመደበኛነት መጠቀም ከሚችለው ውጭ (ከትከሻው በላይ) ወደ ላይ ከፍ አድርጎ አልያም ወደ ጎን ሰፋ አድርጎት (በዚህ ጊዜ ሰውነቱ ከተፈጥሮው ውጭ ገዝፏል ወይም ተጨማሪ ቦታ ይዟል) በዚህ ሂደት ኳሱ እጁን ከነካው የፍጹም ቅጣት ምት ይሰጣል።

ሌላው ቢቀር ከዚህ ቀደም አጨቃጫቂ የነበረውና አንድ ተጫዋች ቅጣት ምት ሲመታ እጁን ወደ ኋላ አጣምሮ በቆመበት ኳሷ እጁን ብትነካው እንደ ቦታው ቅጣት አልያም የፍጹም ቅጣት ምት ይሰጥበታል።

ይህም የሚሆነው ተጫዋቹ እጁን ወደ ኋላ ሲያጣምር ክርኑ በሰውነቱ ትይዩ ስለማይሆን ከተፈጥሮው ውጭ ሰውነቱን እንዳገዘፈና እንዳሰፋ ስለሚቆጠር ነው።

በተጨማሪም በማወቅም ይሁን በአጋጣሚ በእጅ የተቆጠረ ጎልም ይሁን ለጎል ተመቻችቶ የቀረበ ኳስ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ አይጸድቅም።

ተጫዋቾች እጃቸውን ወይም ክርናቸውን ሳያወዛወዙና ሳያነሱ በመደበኛ ቦታው ሆኖ ኳስ ቢነካቸው ግን ፍጹም ቅጣት ምት አያሰጥም።

ጥፋት ሲሰራ አልያም ጨዋታው በሆነ አጋጣሚ በተቋረጠ ጊዜ ጨዋታውን በድጋሚ ለማስጀመር የሚደረገው ሂደትም ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ከዚህ ቀደም ጨዋታው ተቋርጦ ሲጀመር ሁለት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን በማገናኘትና ኳሱን በማንጠር እንዲሻሙ ተደርጎ ኳሱን ቀድሞ ያገኘ እንዲጠቀምበት ይደረግ ነበር።

በአዲሱ የውድር ዘመን ግን ይህ አካሄድ ተቀይሮ ጨዋታው በድጋሚ ሲጀመር ከመቋረጡ በፊት ኳሱን ለመጨረሻ ጊዜ የያዘ ቡድን ካቆመበት ስፍራ ጨዋታውን እንዲጀምር ይደረጋል፤ የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ከሆነ ደግሞ ግብ ጠባቂው ኳሱን ያስጀምራል።

ከዚህ ቀደም ዳኛው ጨዋታውን ቀድሞ የሚጀምረውን ቡድን ለመለየት በተደረገው ሂደት ዳኛው ወደ ላይ የወረወሩትን  ሳንቲም ያሸነፈው ቡድን ጨዋታውን ለመጀመር የሚመቸውን የሜዳ ክፍል ብቻ ይመርጥ ነበር።

በአዲሱ የውድድር ዘመን ግን ወደ ላይ የተወረወረውን ሳንቲም ያወቀው ቡድን የሚመቸውን የሜዳ ክፍል አልያም የኳሱ ጀማሪ የመሆን እድል ይኖረዋል።

ከዚህ ባለፈም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተከታታዮፐች ዘንድ የተለመደው አጭር የግማሽ አመት እረፍት በዘንድሮው አመት የሚቀየር ይሆናል።

እረፍቱ የካቲት ወር ላይ ለሁለት ሳምንት የሚኖር ሲሆን፥ በአንደኛው ሳምንት 5 ጨዋታዎች ሲደረጉ በ2ኛው ሳምንት ደግሞ ሌሎች 5 ቀሪ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

 

 

You might also like
Comments
Loading...