Fana: At a Speed of Life!

ቫይታሚን ኤ የቆዳ ካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ ተጠቆመ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ1 ፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቆዳ ካንሰርን ለመከላከል የፀሃይ ብርሃን መከላከያ (ሰን ስክሪንን) ጨምሮ በርካታ ነገሮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል።

ተመራማሪዎች ከሰሞኑ ይፋ ባደረጉት ጥናት እንዳስታወቁት ከሆነ ደግሞ ቫይታሚን ኤን አብዝቶ መጠቀም ለቆዳ ካንሰር የመጋለጥ እድልን ለመከላከል ይረዳል።

በአሜሪካ በ125 ሺህ ሰዎች ላይ የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ቫይታሚን ኤን አዘውትረው የሚሰውዱ ሰዎች ለቆዳ ካስነር የመጋለጥ እድላቸው የቀነሰ ነው።

የጥናቱ ተሳታፊዎች አብዛኛውን ቫይታሚን ኤ ያገኙት ደግሞ ከሚመገቡት ምግብ መሆኑንም ነው ጥናቱ ያመላከተው።

በብራወን ዩኒቨርሲቲ የዴርማቶሎጂ እና ኤፒዲሞሊጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ኤንዮንግ ቾ እንደተናገሩት፥ የጥናቱ ውጤት አትክልት እና ፍራፍሬ የበዛበት ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል ጠቃሚ እንደሆነ ያረጋግጣል ብለዋል።

በተለይም ደግሞ ከአትክልት እና ፍራፍሬዎች የሚገኘው ቫይታሚን ኤ የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትል በመሆኑ ደህንነቱ አስተማማኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ታዲያ ስለ ቫይታሚን ኤ ጠቀሜታ ይህንን ካልን፤ የቫይታሚን ኤ ምንጭ የሆኑ ምግቦችስ የትኞቻ ናቸው ካላችሁ፦

ስኳር ድንች፣ ካሮት፣ ቆስጣ፣ ብሮኮሊ፣ ማንጎ፣ ዱባ እና ቲማቲም እንዲሁም አሳ እና ስጋ የቫይታሚን ኤ ምንጭ የሆኑ ምግቦች መሆናቸውም በጥናቱ ተመላክቷል።

ተመራማሪዎቹ አክለውም በቫይታሚን ኤ የበለፀጉ ምግቦችን መውሰድ የቆዳ ካንሰር ተጋላጭነትን ይቀንሳል እንጂ ሙሉ በሙሉ አይከላከልም ብለዋል።

ስለዚህ ቆዳችንን ሙሉ በሙሉ ከቆዳ ካንሰር ለመከላከል በቫይታሚን ኤ ከበለጸጉ ምግቦች በተጨማሪ ቆዳችን ለፀሃይ በብዛት አንዳይጋለጥ ጥላ ያለበት ስፍራን ማዘውተር፣ ጸሃይ የማያስገቡ ወፈር ያሉ ለብሶችን መልበስ እና በተጨማሪም ከተገኘ የፀሃይ መከላከያ ቅባት (ሰን ስክሪን) መቀባትን መክረዋል።

ምንጭ፦ www.upi.com/Health

You might also like
Comments
Loading...