Fana: At a Speed of Life!

በ2012 በጀት ዓመት በገጠር የስራ ዕድል ዘርፍ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2012 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በገጠር የስራ ዕድል ዘርፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የብሄራዊ የኢንቨስትመንትና የስራ ዕድል ፈጠራ መሪ ኮሚቴ ስራን በያዝነው ወር መጀመሪያ  ላይ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የብሄራዊ ኮሚቴው የ2012 የበጀት ዓመት ቀዳሚ ጉዳይም ስራና ስራ ፈላጊን በተገቢው ሁኔታ ማገናኘት ነው።

በዚህ መሰረትም በየዓመቱ ከ2 እስከ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ወጣቶቸ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በማሰማራት የስራ ዕድል ለመፍጠር  የሚሰራ መሆኑን  ኮሚቴው ይፋ አድጓል።

ችግሩን ለመፍታት ከተመረጡት ዘርፎች መካከልም የግብርናው ዘርፍ ቀዳሚ ሲሆን፥ የማዕድን፣ ቱሪዝምና ኢንፎርሜን ቴክኖሎጂ  ዘርፎች ደግሞ በተከታይነት ተቀምጠዋል።

የግብርና ሚኒስተር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ፥ ሚኒስቴሩ በ2012 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በገጠር የስራ ዕድል ዘርፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር ሃላፊትነት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፍ ባለፉት 3 ዓመታት ለ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ያነሱት ዶክተር ካባ፥ በኮሚቴው የተጣለብንን ሃላፊነት ለመወጣት ከክልሎች ጋር የዕቅድ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ማቲዎስ አኒዮ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ132 ሺህ ዜጎች ብቻ የስራ እድል በመፈጠር ዝቅተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል።

በ2012 ግን እስከ ቀበሌ መዋቅር በወረደ የእቅድ ዝግጅት በገጠር ያሉ የስራ አድል አማራጮችና አቅሞችን በመለየት ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ ለ605 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ይሰራል ነው ያሉት።

የአፋር ክልል የግብርና ቢሮ የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ መሀሙድ አህመድ በበኩላቸው፥ ዘርፉ አዲስ በሆነበት ክልል የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የስራ አጥ ልየታ መደረጉን አንስተዋል።

በተለይም በክልሉ ካለው  የመስኖ ልማት ስራዎች ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር የተመረቁትን ወደ ስራ ለማሰገባት ታስቧል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ፥ የክልሉ ሁሉም ሴከተሮች ባላቸው የስራ እድል መፍጠሪያ ፕሮግራሞች ዜጎችን ተጠቃሚ  ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ በተጠናቀቀው በጀት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ተመቻችቶ የ5 ቢሊየን ብር የገበያ ትስሰር መፈጠሩን አስታውሰዋል።

በገጠር ስራ እድል ፈጠራው  የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻልና በግብርና የሚሰማሩ ኢንቬስተሮችን በማበረታታት እቅዱን ማሳካት ይጠበቃል ብለዋል ።

በሃይለየሱስ መኮንን

 

You might also like
Comments
Loading...