Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በማህበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለሚፈልጉ ዜጎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በማህበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለሚፈልጉ ዜጎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ከተሞች እና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ምስራቅ ተፈራ እንደተናገሩት በከተሞች እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት የመገንባት ፍላጎት ለመፍታት ቢሮው የተለያዩ የመሬት አሰጣጥ እና የግንባታ አማራጮችን እየተገበረ ቢገኝም በሚፈለገው ልክ አይደለም ብለዋል፡፡

ምክትል ሃላፊው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር እና በከተሞች የመሬት ሀብት ውስን መሆን የችግሩ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የከተሞችን እድገት እና የዜጎችን ፍላጎት ለመፍታት እንዲሁም ውስን የሆነውን የከተማ መሬት በቁጠባ ለመጠቀም እንዲቻል የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማትን ማፋጠን የከተሞችን እድገት ከጎን ወደ ላይ ለማድረግ እና የመሰረተ ልማት አቅርቦቱን ምቹ ለማድረግ ተመራጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሰረት በማህበር ተደራጅተው ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን በማቀናጀት የጋራ መኖሪያ ቤት ለሚፈልጉት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡

በማህበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚፈልጉት ዜጎችም ለግንባታው ከሚያስፈልገው ወጪ 20 በመቶ መቆጠብ አለባቸው ተብሏል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like
Comments
Loading...