Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ መንገዶች ላይ የፍጥነት መገደቢያ በመሰራታቸው የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ እንደተቻለ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከተማዋ በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ በሚከሰትባቸው መንገዶች ላይ የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎችን በመስራት አደጋዎችን መቀነስ እንደቻለ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂሬኛ ሂርጳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት በከተማዋ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ መንስኤዎችን ጥናት ተካሂዷል፡፡

በዚህም ለአደጋዎች ከተፈቀደላቸው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር ምክንያት በሆነባቸው የተወሰኑ መንገዶች ላይ የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች እንደተሱ ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በ2010 በጀት ዓመት 80 እና በ2011 በጀት ዓመት ደግሞ 150 የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች በከተማዋ ለፍጥነት ተጋላጭ በተባሉ መንገዶች ላይ እንደተሰሩ ገልፀዋል፡፡

የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች ከተሰሩባቸው መንገዶችም የወሰን፣ የካራ ፣ ከኮከበ ጸባህ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት አፍንጮ በርና መካንሲ አከባቢዎች ይገኙበታልም ብለዋል።

በእነዚህ መንገዶች የፍጥነት መገደቢያ ጉብታዎች ከመሰራታቸው በፊት በዓመት በአማካይ 32 ሰዎች ይሞትባቸው ነበረ ተብሏል፡፡

ጉብታዎቹ ስራ ላይ በዋሉባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በመንገዶቹ ሁለት ሰዎች ብቻ በፍጥነት ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በሰብለወርቅ ኤልያስ

You might also like
Comments
Loading...