Fana: At a Speed of Life!

በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት የተሰማሩ ሶስት የልማት ድርጅቶች 134 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር አተረፉ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ፣ 1 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት መስክ የተሰማሩ ሶስት የልማት ድርጅቶች 134 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ማተረፋቸው ተገለፀ፡፡

ድርጅቶችም የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ፣ የፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት እና የግዮን ሆቴል ድርጅት ናቸው።

በ2011 በጀት ዓመት ባጠቃላይ 138 ነጥብ 6 ሚሊየን ለማትረፍ አቅደው የነበሩት ድርጅቶቹ፥134 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ማትረፍ መቻላቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ድርጅቶቹ ይህንን ትርፍ ማግኘት የቻሉት ካቀዱት 739 ነጥብ 77 ሚሊየን ብር ሽያጭና አገልግሎት 683 ነጥብ 55 ሚሊየን በማከናወናቸው እንደሆነ አቶ ወንዳፍራሽ ገልፀዋል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት በ2011 በጀት ዓመት ከሽያጭና አገልግሎት 501 ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 469 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር አግኝቷል ብለዋል ።፡

ይህ ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ7 ነጥብ 77 በመቶ ብልጫ አለው ነው ያሉት ፡፡

በትርፍ ረገድ ደግሞ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ከታክስ በፊት ብር 75 ነጥብ 4 ሚሊየን ለማትረፍ አቅዶ ብር 75 ነጥብ 6 ሚሊየን ማትረፍ ችሏል፡፡

በውጭ ሽያጭ ረገድ ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ 14 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 13 ነጥብ 3 ሚሊየን ማግኘት እንደቻለ ተጠቁሟል፡፡

ሌላው የግዮን ሆቴል ድርጅት ሲሆን ሆቴሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 86 ነጥብ 77 ሚሊየን ብር የአገልግሎት ሽያጭ በማከናወን ከታክስ በፊት 81 ነጥብ 65 ሚሊየን ብር ሽያጭ አከናውኗል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ከታክስ በፊት ብር 33 ነጥብ 2 ሚሊየን ትርፍ ማግኘት እንደቻለ ተጠቁሟል፡፡

የፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅትም በተመሳሳይ 152 ሚሊየን ብር የአገልግሎት ሽያጭ ለማከናወን አቅዶ 132 ሚሊየን ብር ማሳካቱን አቶ ወንዳፍራሽ ገልጸዋል።

በትርፍ ረገድ ፍልውሃ ደርጅት ከታክስ በፊት 25 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ማትረፍ መቻሉን ገለጸዋል።

በታሪከ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...