Fana: At a Speed of Life!

ሰነዶችን ማረጋገጥ የሚቻልባቸው የቆንስላ ጉዳዮች ጽህፈት ቤቶች በአራት ክልሎች ሊከፈቱ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወደ ውጭ ሀገራት ለመሄድ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ለማረጋገጥ የሚቻልባቸው የቆንስላ ጉዳዮች ጽህፈት ቤቶች በሀገሪቱ አራት ክልሎች ሊከፍት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ጋር በፈረመቻቸው የስራ ስምሪቶች ምክንያት የሰነድ ይረጋገጥልኝ ጥያቄዎች መብዛታቸውን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ጽህፈት ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመክፈት መወሰኑን ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚሰጣቸው የትምህርት፣ የልደትና የጋብቻ ሰነድ ህጋዊ ማረጋገጫ አገልግሎት በተጨማሪ የውጭ ሀገራት ስራ ስምሪቱ ጫና መፍጠሩን፥ በሚኒስቴሩ የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ሸዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ይህንን ጫና ተቋቁሞ ለመስራትም የአገልግሎት መስጫ መስኮቶችን ቁጥር በመጨመርና አገልግሎቶችን በቀናት በመከፋፈል ለመስራት ቢሞከርም፥ ከሁሉም ክልሎች የስራ ስምሪት የሚፈልጉ ዜጎች ወደ ተቋሙ በመምጣታቸው ችግሩን ሰፊ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅርንጫፍ የአገልግሎት መስጫዎችን በአራት ክልሎች ለመክፈት ከክልሎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል ብለዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ በኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች የሚከፈቱ ሲሆን፥ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።

እስከዚያው ድረስም የተገልጋዮችን እንግልት ለመቀነስ የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን በተቋሙ የማከናወን ስራ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ላይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በተገልጋዮች ቅሬታ እየቀረበበት ይገኛል።

በትእግስት ስለሺ

You might also like
Comments
Loading...