Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሶስት ዓመታት የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ተደራሽነት 50 በመቶ ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 26፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ሶስት ዓመታት የእናቶች በጤና ተቋማት የመውለድ ተደራሽነት 50 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደገለጹት ባለፉት ሶስት ዓመታት እናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ እንዲወልዱ የማድረግ ስራ 50 በመቶ ደርሷል።

በዚህም የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳን 50 ከመቶ ማድረስ መቻሉን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

ተግባሩን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠልም በአሁኑ ወቅት በጽንስ ውስጥ ያለን ህጻን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚስችሉ 3 ሺህ 500 የህክምና መሳሪያዎች ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም 300 የአልትራሳውንድ መሳሪያዎች ግዥ ተፈፅሞ በቅርቡ ለጤና ጣቢያዎች ማሰራጨት የሚጀመር መሆኑን አንስተዋል።

የጤና ባለሙያዎች በስነ ምግባር ታንጸው በተገቢው ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተወሰኑ ጤና ጣቢያዎች በተቋማቸው መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት ወደ ሆስፒታል ሪፈር በማድረጋቸው የተነሳ ሆስፒታሎች ላይ መጨናነቅ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ይህን ችግር ለማሻሻልም በአሁኑ ወቅት በጤና ጣቢያዎች የማሻሻያ ስራ መጀመሩንም አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም በ10 ጤና ጣቢያዎች ላይ በተደረገ የሙከራ ስራ ውጤት ማስገኘቱን አመላክተዋል።

ማሻሻያው በቀጣይ 2012 በጀት ዓመት በሁሉም ጤና ጣቢያዎችና በክልሎች ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...