Fana: At a Speed of Life!

ሁዋዌይ አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተምን በሩሲያው አውሮራ ለመተካት እንደሚፈልግ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 22፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይናው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ሁዋዌይ ለሚያመርታቸው ስማርት ሰልኮች፣ ታብሌሎች እና ሌሎች መገልገያዎች በአሜሪካ የበለፀገውን አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ነው የሚጠቀመው።

አሁን ግን አሜሪካ ሁዋዌይ በአሜሪካ ውስጥ የበለፀጉ ቴክኖሎጂዎችን እንዳይጠቀም በተደጋጋሚ እገዳ እየተጣለበት መሆኑን ተከትሎ ፊቱን ወደ ሌሎች ሀገራት ሊያዞር እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ኩባንያው ፊቱን ሊያዞር ካሰባቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ ሩሲያ ነች የተባለ ሲሆን፥ በአውሮፓውያኑ 2020 ለሚካሄደው የሩሲያ የህዝብና ቤት ቆጠራ ጥቅም ላይ ለሚውሉ ሁዋዌይ ታብሎቶችም አውሮራ የተባለውን በሩሲያ የበለፀገ ኦፕሬቲንግ ሲስተም መጠቀሙ ነው የተነገረው።

ኩባንያው ከዚህ በዘለለም ወደፊት የሚያመርታቸው የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ላይ በስፋት የመጠቀም እቅድ እንዳለው ነው የተነገረው።

የኩባንያው ቃል አቀባይ፥ ሁዋዌይ በሩሲያው ፕሮጀክት ደስተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ አውሮራ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የተገጠመላቸውን ታብሌሎች ለማሳያ አቅርቧል ብለዋል።

አውሮራ የተባለው ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሩሲያ መንግስት ቴሌኮሙዪኒኬሽን ኩባንያ የሆነው ሮስቴሌኮም ኩባንያ ንብረት ነው።

ሮስቴሌኮም እና ሁዋዌይ በጋራ እየሰሩት ያለው ፕሮጀክት በእቅዱ መሰረት ከሄደ ሁዋዌይ በ360 ሺህ ታብሌቶች ላይ አውሮራ ኦፕሬቲንግ ሲስተመን በመግጠም ለሩሲያ የሚያቀርብ ይሆናል።

ይህም ሁዋዌይ አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተምን በአውሮራ ለመተካት ለሚሰራው ስራ እንደ እንድ እርምጃ እንደሚቆጠር ነው የተገለፀው።

ከዚህ በተጨማሪም ሁዋዌይ ከዚህ ቀደም በራሱ ያበለፀገውን ሀርሞኒ የተባለ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።

ምንጭ፦ fossbytes.com

You might also like
Comments
Loading...