Fana: At a Speed of Life!

ሀገር አቀፍ የፍትህ ቀን የፊታችን ጳጉሜን 5 ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 14፣ 201 1(ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሀገር አቀፍ የፍትህ ቀን የፊታችን ጳጉሜን 5 ቀን የሚከበር መሆኑን አስታውቋል።

የኢፌዴ.ሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን ሀገር አቀፍ የፍትህ ቀን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ፥ የዘንድሮው የፍትሕ ቀን “እኔ ለፍትሕ ተገዢ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።

የፍትህ ቀንን ማክበር ያስፈለገውም በዓሉን ስናከብር በሀገራችን በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ የተጀመረው ለውጥ የዘርፉን ተስፋ ያለመለም ቢሆንም አሁንም ያሉብንን ተግዳሮቶች ለመለየት የሚያግዝ በመሆኑ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምትሆን በነፃነት፣ በፍትህ ተምሳሌትነት እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት፣ አዳዲስ አሰራሮችን፣ የሕግ ማህቀፎችን በማሻሻል አንፀባራቂ የለውጥ ድሎች በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የፍትህ ቀንን ማክበር የትናንት የፍትህ ማነቆዎቻችን በማስወገድ የዛሬ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ለቀጣይ ትውልድ የሚሆን ጽኑ መሰረት ያለው ትሩፋት መኖርን ለማመላከት ያስችላል ነው ያሉት።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የፍትህ ተቋማት የተጣለባቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ዘመናዊ የሆነ የፍትህ አስተዳደር ለመገባት ከህብረተሰቡ ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጎልበት፣ የህዝብን የነቃ ተሳትፎ በመጠቀም ዋስትና ያለው ፍትህ መገንባት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፍትህ ቀን በዓል የፍትህ አካላት የህዝብ አመኔታ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ግብዓቶችን ከህዝቡ ለማሰባሰብ፣ ህብረተሰቡ በፍትህ ሥርዓቱ ሂደት አጋርና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል መነሳሳት መፍጠር እና ሌሎች መሰል ተልዕኮዎችን ያነገበ መሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል።

በዓሉ በፍትህ ስርዓቱ የታዩ ለውጦችና ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በቀጣይ ያሉ ተልዕኮዎችን የሚገልጽ ሰነድ ተዘጋጅቶ በ9ኙ ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አሰተዳደሮች ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ የውይይት መደረኮችን ተዘጋጅተው ውይይት የሚደረግበት መሆኑም ተመላክቷል።

እንዲሁም የተለያዩ አውደ ርዕዮችና የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በማካተት ለህብረተሰቡ አስተማሪና አዝናኝ ዝግጅቶች ይቀርባሉ ነው የተባለው።

ጳጉሜን 5 በሚከበረው የመዝጊያና የምስጋና ፕሮግራም ላይም ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድረሻ አካላት፣ ጥሪ የሚደረግላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ከክልል የሚመጡ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በፕሮግራሙ ለሀገራዊ አንድነት ለሰላምና ለፍትህ ሥርዓቱ መጎልበት አሰዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች የዕውቅና ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል።

You might also like
Comments
Loading...