Fana: At a Speed of Life!

ደመወዛቸውን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ቦንድ እየገዙ ያሉት አዛውንት

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 12፣2011 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ፋንታ መስተሳህል የተባሉ አዛውንት የህዳሴ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ በጡረታ ደመወዛቸውን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ እየገዙ መሆኑ ተነግሯል።

አቶ ፋንታ ኢትዮጵያን አንስተው የሚጠግቡ አይደሉም፤ ኢትዮጵያዊነት ከዜግነት ከፍ ያለ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ደም፣ አጥንት፣ ስጋ እና መንፈስ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት በቃል የማይነገር በስሌት የማይመረመር ሲኖሩት ብቻ የሚጣፍጥ ምርጫ ብቻ ሳይሆን ስጦታ የሆነ ክብር ነው፤ በኢትዮጵያውያን የማይቀኑ አይኖሩም።

የኢትዮጵያውያን እሴቶች የተናወጠን ሀገር ያበርዳሉ። የኢትዮጵያውያን ደግነት ከአለት የጠጠረን ክፉ ልብ ያለዝባል። የኢትጵያውያን አንድነት የማይረታው ኃይል የማይገፋው ተራራ፣ የማይሻገረው ድልድይ የማያልፈው መከራ የለም። ኢትዮጵያውያን ሲከፉም ሆነ በጎ ሲሆኑ ለሀገራቸው እሴት ተጨንቀው ለሀገራቸው ህልውና ቆመው ነው። በኢትዮጵያ ምሎ ኢትዮጵያን በትልቁ ስሎ አፍሮ የተመለሰ የለም። ይልቁንስ አሸንፎ በድል ይመለሳል እንጅ፤ እነዚህ ሁሉ የአዛውንቱ እምነት ናቸው።

ፋንታ መስተሳህል በ1942 ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ከደብረ ማርቆስ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኝ ወንቃ ጊዮርጊስ በምትባል የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው የተወለዱት። ያደጉበት አካባቢ በደግነት አንፆ በሀገር ፍቅር ቃል ኪዳን አስገብቶ ገንብቷቸዋል። የሀገር ፍቅርን በልጅነታቸው ዓይተውታል። ለሀገር መሞት ድል እንደሆነም ተረድተዋል። አቶ ፋንታ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው የደብረማርቆስ ከተማ ተጉዘው በንጉሥ ተክለሃይማኖት ትምህርት ቤት ትምህርት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተከታተሉ።

አቶ ፋንታ የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ጊዜ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ስር በአውራጎዳና ተቀጥረው ወደ ኢሊባቡር ተጓዙ። ስራቸውን ጎን ለጎን እያስኬዱ በበደሌ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሥራ የጀመሩት አቶ ፋንታ ከጀማሪ ሠራተኛነት እስከ የመንገድ ጥገና ሥራ ኃላፊነት ከ36 ዓመታት በላይ በብቃት አገልግለዋል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የሥራ ዘመናቸው መንገድ ዓይተው የማያውቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን መንገድ እየጠረጉ አገናኝተዋል። ተራርቀው በፍቅር የሚተሳሰቡትን ወገኖች በመንገድ አገናኝተው የበለጠ ፍቅራቸው እንዲፀና አድርገዋል። እኝህ ሰው በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በጅማ ዲስትሪክት ለበርካታ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ የሥራ ቦታ ቀይረው ወደ ጎንደር አቀኑ።

ጎንደር በቆዩባቸው ጊዜያትም የተለመደውን ጠንካራ ሥራቸውን አከናወኑ። ‹‹ችግርን በፅናት ለማለፍ ጥረት አደርጋለሁ፤ ሥራ እወዳለሁ እንጅ እረፍት አልወድም›› ብለዋል አቶ ፋንታ የግል የሥራ መመሪያቸውን ሲነግሩን። አቶ ፋንታ በእነዚህ የሥራ ዘመኖቻቸው የዓባይ ወንዝ ያለአገልገሎት መፍሰስ ያበሳጫቸው እንደነበርም ነግረውናል።

ዓባይ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ወንዞች የሚገብሩለት የሱዳን እና የተለያዩ የተፋሰሱ ሀገራት የሚሳሱለት የወንዞች ሁሉ ንጉሥ ነው። ትውልዱና ዕድገቱ ኢትዮጵያ ነው። የዓባይ የዘመናት ጉዞ አቶ ፋንታን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በቁጭት ሲያሳርር ቆይቷል። አቶ ፋንታ የዓባይ ግድብ መሠራት ከጀመረበት አንድ ዓመት ቀደም ብለው ከ36 ዓመታት በላይ የሠሩበትን ሥራ በጦሬታ ተሰናብተው በትውልድ ቦታቸው ደብረ ማርቆስ ኑሯቸውን አድርገው ነበር።

ያ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሲያንገበግባቸው የነበረውን ዓባይን ‹‹ለኢትዮጵያውያን እንዲገብር ልናደርግ ነው›› ሲባሉ በደስታ ተነሱ። ከምትከፈላቸው የጦሬታ 1ሺህ 600 ብር 1ሺህ ብሩን ለዓባይ ሰጥተው በ600 ብር ጎጇቸውን መምራት ጀመሩ። ከተጀመረበት ዘመን አንስተው እስካሁን ድረስ ቃላቸው አልታጠፈም፤ ከወር የጦሬታ ደመወዛቸው ከፍ ያለውን ለዓባይ እየሰጡ ለዓመታት ዘለቁ፤ አሁንም ቃላቸውን እንዳከበሩ እስከ ፍጻሜ ቀጥለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጓተት ቢበሳጩም በበርካታ የመንገድ ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ መጓተቶችን እያዩ ለዘመናት ኖረዋልና ‹‹በሥራ ጊዜ የሚያጋጥም ችግር ነው፤ ከዚህ ፕሮጀክት መጓተትና መሠል ክፍተት ባልጠብቅም ከመናደድ ያለፈ ቃሌን የሚያሽር ሆኖ ስላላገኘሁት እስኪጠናቀቅ ድጋፌን እቀጥላለሁ›› ብለዋል፡፡

አቶ ፋንታ ጤንነታቸው የተሟላ አይደለም፤ የስኳር ሕመምተኛ ናቸው። የሕክምና ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ሕይወታቸው ከዓባይ እንደማይበልጥባቸው ነው የነገሩን። አቶ ፋንታ ‹‹ዓባይ ተገድቦ የመጀመሪያውን መብራት ዓይቼ ብሞት ለኔ ደስታዬ ነው›› ሲሉም ነግረውናል። ዓባይ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መለኪያ እንደሆነም ያምናሉ። ይህ ትውልድ አልፎ ሌላ ትውለድ እስኪተካ ድረስ ዓባይ ሳይጠናቀቅ ቢቆይ እንኳ ቀጣዩ ትውልድ ይጨርሰዋል የሚል የፀና እምነትም አላቸው።

‹‹ኢትዮጵያውያን ይለያያሉ፤ ኢትዮጵያ ትፍርሳለች ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፤ ለኢትዮጵያውያን ከሰማይ የተላከ ቃል ኪዳን አለ›› ሲሉም በኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ዘላለማዊነት ያላቸውን የፀና እምነት ተናግረዋል። በዓባይም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ለሚመጣው ችግር ተምሮ በፅናት ማለፍ እንጂ ተሸቅቆ ወደኋላ መመለስ እንደማይገባም ይመክራሉ። ቆራጥነት እና ሕዝብን ለአንድነት ማስተባበር እንደሚገባም አሳስበዋል። ለ6 ዓመት የገዙትን ቦንድ ሌሎች ሲቀበሉ እርሳቸው ግን ድጋሜ እየገዙበት ነው። ይህንንም ‹‹የሕዳሴ ግድቡ ተጠናቀቀ›› እስኪባል ድረስ እንደማያቋርጡ ነግረውናል። ሌላውስ በሀገሩ ላይ ምን ያክል የፀና እምነት አለው? ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትስ ምን ያክል ዝግጁ ነው? ሠላም፣ ፍቅር እና አንድነት በኢትዮጵያ ምድር ይዝነብ። ኢትዮጵያውያንንም በእኩልነት ያብቅል።

ምንጭ ፦አብመድ

 

You might also like
Comments
Loading...