Fana: At a Speed of Life!

የ2012 የፌደራል መንግስት በጀት 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር ሆኖ ፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 1፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2012 በጀት ዓመት የቀረበውን 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር የፌዴራል መንግስት በጀት አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ባለፈው ሰኔ 1 ቀን በሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ በዛሬው እለት አጽድቆታል።

ከጸደቀው በጀት ውስጥም 109 ቢሊየን 468 ሚሊየን 582 ሺህ 456 ብር ለመደበኛ ወጪዎች ይውላል።

ለካፒታል ወጪዎች ደግሞ 130 ቢሊየን 710 ሚሊየን፣ 876 ሺህ 568 ብር የሚውል ይሆናል።

በተጨማሪም 140 ቢሊየን 775 ሚሊየን 506 ሺህ 265 ብር ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና 6 ቢሊየን ብር ደግሞ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፅሚያ ድጋፍ ይውላል ተብሏል።

በጀቱ ከአምናው የበጀት አመት ጋር ሲነጻጸር የ40 ቢሊየን ብር ጭማሪ አለው።

የካፒታል በጀት ወጪ አሸፋፈኑ ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢ 94 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ቀሪው ከውጭ ሀገር የሚገኝ ብድርና እርዳታ ሌሎች ገቢዎች የሚገኝ ሲሆን፥ ቅድሚያ ለተሰጣቸው ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ ግብርና እና የከተማ ልማት ወጪዎች ይሆናል።

ከመደበኛ ወጪው 109 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ውስጥ 34 በመቶው የደሞዝ አበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች፣ ቀሪው 66 በመቶ ለብድር ክፍያ፣ ለልዩ ልዩ ወጪዎችና ለሌሎች ክፍያዎች የሚውል ነው።

386 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለመንግስት 2012 በጀት አመት ወጪ ሲታቀድ የመንግስት ገቢ ደግሞ በተመሳሳይ 289 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ይሆናል ተብሎ ነው የታሰበው።

You might also like
Comments
Loading...