Fana: At a Speed of Life!

የ15 ዓመት የቡና ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ15 አመት የቡና ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ፍኖተ ካርታው በቡና ምርት እና ምርታማነት፣ ግብይት እንዲሁም እሴት መጨመር ላይ እና በቡና ውጭ ንግድ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ መዘጋጀቱን ባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የግብይት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሻፊ ኡመር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የቡና ወጭ ንግድ ተግዳሮቶች ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ምክንያቶችንም በሚፈታ መልኩ መዘጋጀቱን ነው አቶ ሻፊ ኡመር ያብራሩት።

ለአብነትም በአሁኑ ሰአት ወደ ውጭ ከሚላከው ቡና እሴት ተጨምሮ የሚላከው ከ1 በመቶ አይበልጥም ብለዋል አቶ ሻፊ።

በፍኖተ ካርታው ግን እሴት ተጨምሮ የሚላከውን ቡና እስከ 15 በመቶ እና ከዚያ በላይ ለማድረስ ተቀምጧል ብለዋል።

የቡና ግብይት እና ምርታማነት በቀጣይ 15 ዓመት የት መድረስ አለበት የሚለውም በፍኖተ ካርታው ከተቀመጡ በርካታ ጉዳዮች ተጠቃሽ ነው።

አቶ ሻፊ ፍኖተ ካርታው በቀጣይ ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like
Comments
Loading...