Fana: At a Speed of Life!

የኩንሻን ከተማ ኩባንያዎች በድሬዳዋ ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይናዋ ኩንሻን ከተማ የሚገኙ ኩባንያዎች በድሬዳዋ ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት መዘጋጀታቸውን አስታወቁ።

በከተማዋ ከንቲባ ዙ ዩ ዶንግ የተመራ የመንግሥትና የባለሃብቶች ቡድን ትናንት በድሬዳዋ ጉብኝት ካደረገ በኋላ፥ ኩባንያዎቹ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ለመመስረት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ግንባታው በሁለት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቀው ፓርክ ለበርካታ ወገኖች ሥራ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ኩባንያዎቹ ፓርኩን ለመገንባት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማሳካት እገዛ ይደረጋል ብለዋል።

ኩባንያዎቹም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የወጣቶች የክህሎት ማሰልጠኛ ተቋም በመገንባት ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ፥ የኩባንያዎቹ እርምጃ ከሥራ ዕድል ፈጠራ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ – ዩኒቨርሲቲ ትስስርን ለማጠናከርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማጎልበት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የከተማዋ ከንቲባና የልዑካን ቡድን አባላቱም የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ የሃገሪቱን ኢንዱስትሪ ልማት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

 

You might also like
Comments
Loading...