Fana: At a Speed of Life!

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ተጨማሪ ታሪፍ በፈረንሳይ መጣሉን ተከትሎ አሜሪካ ምርመራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 4 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ተጨማሪ ታሪፍ በፈረንሳይ መጣሉን ተከትሎ  ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ የንግድ ተወካዮች ውሳኔው ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የአሜሪካ ካምፓኒዎችን  ኢላማ ያደረገ እና አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፈረንሳይ ፓርላማ ጎግልና ፈስቡክን በመሰሉ በሀገሪቱ በሚገኙ ኩባንያዎች ላይ የተጨማሪ የ3 በመቶ ታሪፍ እንዲጣልባቸው ውሳኔ አሳልፏል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎቹ አለም አቀፍ የታክስ ስርዓትን እየተላለፉ ይገኛሉ ስትል ፈረንሳይ ቅሬታ አቅርባለች፡፡

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ ዋና መስሪያ ቤቶቻቸውን ከፍተኛ ትርፍ እና  ዝቅተኛ ታክስ ወደ ሚጠየቁበት ሀገራት ማዘዋወር ይችላሉ ተብሏል፡፡

ውሳኔው ከ750 ሚሊየን ዩሮ በላይ ትርፍ ያላቸው እና ከትርፍ መከካከል 25 ሚሊየን ዩሮውን በፈረንሳይ የሚያገኙት  የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ይመለከታል ተብሏል፡

ዶናልድ ትራምፕም ይህ የታክስ ውሳኔ ሊያሳድረው ስለሚችለው ተፅዕኖና ፍትሃዊነት በተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የዚህ ምርመራ ውጤትም ትራምፕ በሌሎች ሀገራት ላይ  የጣሉትን አይነት ታሪፍ በፈረንሳይ ላይም እንዲጥሉ ምክንያት ሊሆን ይችላል ነው የተባለው፡፡

ይህም አሜሪካ እና ፈረንሳይ   ወደ ንግድ ጦርነት እንዳትገባ ስጋትን ፈጥሯል፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like
Comments
Loading...