Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳን ለተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያን አደነቀ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 2፣ 2011(ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳን ለተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ አደነቀ።

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 41ኛው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለፃ ተደርጓል።

ገለፃውን ያቀረቡት በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ ዶክተር አንድሪው ጊልሞር እና በሱዳን የፍትህ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች አማካሪ ጽህፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ኦሳማ ሄሜይዳ ናቸው።

ይህንን ተከትሎም በርካታ አባል ሀገራት ጉዳዩን አስመልክተው ንግግር ማድረጋቸው ተገልጿል።

በዚህም በአፍሪካ ህብረት እና በኢትዮጵያ የተመራው ድርድር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሐመሌ 5 ቀን 2019 በሱዳን በተፈረመው ስምምነት ስኬት ማስመዝገቡ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ በጄኔቫ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛአምባሳደር ዘነበ ከበደ የሀገራቸውን አቋም እና በድርድሩ ሂደት ኢትዮጵያ የነበራትን ሚና አስመልክቶ ንግግር ማድረጋቸውን በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like
Comments
Loading...