Fana: At a Speed of Life!

አዴፓ አቶ ተመስገን ጥሩነህን ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርነት በእጩነት እንዲቀርቡ ወሰነ

አዲስ አባበ ፣ ሃምሌ 8 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ተመስገን ጥሩነህን ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርነት በእጩነት እንዲቀርቡ ወሰነ።

ማእከላዊ ኮሚቴው ለቀናት በባህር ዳር ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባውን ያጠናቀቀ ሲሆን፥ ለተጓደሉ የፓርቲ አመራሮች ቦታዎች ምርጫ አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ተመስገን ጥሩነህንም ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደርነት በእጩነት እንዲቀርቡ ወስኗል።

አቶ ተመስገን ጥሩነህ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒውተር ሳይንስ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋም የለውጥ አመራር ያገኙ ሲሆን፥ በተለያዩ የፌዴራልና የክልል መስሪያ ቤቶች በሃላፊነት አገልግለዋል።

በዚህ መሰረትም የአማራ ክልል የርዕሰ-መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር፣ የኢትዮቴሌኮም ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣በሃገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ኤሌክትሮኒክስ መምሪያ፣ቴክኒካል መረጃ መምሪያ እንዲሁም በሚኒስትር ማእረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/ የማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።

እንዲሁም  አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና አቶ አገኘሁ ተሻገርን የአዴፓ ስራ አስፈፃሚነና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች አባል ሆነው ተመርጠዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like
Comments
Loading...