Fana: At a Speed of Life!

ቦይንግ ለ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የ100 ሚልየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የ100 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ።

ቦይንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኒዢያው ላየን ኤይር ባጋጠመው ሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች ህይወታቸውን ላጡ የ346 ሰዎች ቤተሰቦች እና ተፅዕኖ ለደረሰባቸው ማኅበረሰቦች መደገፊያ የሚውል መሆኑም ታውቋል።

የገንዘብ ድጋፉ በሚቀጥሉት በርካታ ዓመታት የሚሰጥ መሆኑን ያስታወቀው ቦይንግ፥ ገንዘቡን ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦችን እና በአደጋው ጫና የደረሰባቸውን ማህበረሰቦች የትምህርት ወጪ እና ኑሮ ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።

ድጋፉም ከመንግስት ባለሥልጣናት እና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለተጎጂ ቤተሰቦች እንደሚያደርስም ነው ኩባንያው ያስታወቀው።

የቦይንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ፥ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኒዢያው ላየን ኤይር ባጋጠመው ሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች ባለፈው የሰው ህይወት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው አስታውቀዋል።

ለአውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን የተመኙት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ አሁን የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለተጎጂ ቤተሰቦችን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚረዳ እምነታቸውን ገልፀዋል።

ቦይንግ የገንዘብ ድጋፉን ይፋ ያድርግ እንጂ የተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቆች ግን የቦንይግን አንቅስቃሴ ተቃውመውታል።

መቀመጫውን አሜሪካ ቴክሳስ ያደረገው እና የተወሰኑ የተጎጂ ቤተሰቦችን የወከለው ጠበቃ ኖሚ ሁሴን፥ ቦይንግ ይፋ ያደረገው ገንዘብ በአደጋው ምክንያት የተጎዱ ቤተሰቦችን አይክስም ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ በርካታ ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳ አይደለም የሚፈልጉት፤ ከአደጋው ጀርባ ያለውን እውነታ እንጂ ያሉት ጠበቃው፥ ቦይንግ ግን በገበያው ላይ የነበረውን ሽያጭ ወደ ነበረበት ለመመለስ በማለም ድጋፉን ማድረጉን አስታውቀዋል።

ጠበቃ ኖሚ ሁሴን ሰባት የተጎጂ ቤተሰቦችን በመወከል በቦይንግ ላይ ክስ ያቀረቡ ሲሆን፥ ክሶቹ እስከ 276 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ካሳ የሚጠይቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታም ከ50 በላይ ተጎጂ ቤተሰቦች በቦይንግ ላይ የክስ ፋይል መክፈታቸውንም ነው ጠበቃው አያይዘው የገለጹት።

አለም አቀፍ ተንታኞች በበኩላቸው የሁለቱ አደጋዎች መነሻ የቦይንግ የሶፍትዌር ችግር ከሆነ ቦይንግ ለእያንዳንዱ ሟች ቤተሰቦች 1 ሚልየን ዶላር ካሳ መክፈል ይጠበቅበታል ብለዋል።

ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ የነበረ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በጥቅምት ወር ላይ የኢንዶኔዢያው የላየን አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ አውሮፕላን ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት አልፏል።
እነዚህን ሁለት አደጋዎች ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ አውሮፕላኖቹ መቼ ወደ በረራ ይመለሳሉ የሚለውም እስካሁን አልታወቀም።

ምንጭ፦ www.bbc.com

You might also like
Comments
Loading...