Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 11 ወራት ከ50 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩን የኢዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 11 ወራት ከ50 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩን የኢዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የኢዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዛሬው እለት ባለፉት 11 ወራት የዘርፉ አፈፃጸም ላይ ውይይቱን አካሂዷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ባለፉት 11 ወራት ለ50 ሺህ ያህል ዜጎች ቋሚ እና ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ጊዜአዊ የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

ከገቢ አንፃርም ከባለፈው ዓመት ተማሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ100 ፐርሰንት በላይ ብልጫ መመዘገቡንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል፡፡

ከሸድ ኪራይ የሊዝ ገቢና ከአገልግሎት ሽያጮች 316 ሚሊየን ብር የተመዘገበ ሲሆን ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶችም 110 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

አዲስ ስራ በሚጀምሩ የኢንዱስሪ ፓርኮች አካባቢ ውሃና መብራት የሰራተኞች የመኖሪያ ቤት እጥረት የዘርፉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ በውይይቱ ተነሰቷል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ከመፍትሄዎቹ መካከል ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ ከኤሌክተርክ ሃይል በተጨማሪ ሌሎች የሃይል አማራጮችን ለመጠቀም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡

አምራች ኩባንያዎች ለሰራተኞቻቸው መኖሪያ ቤቶችን ለመገነባት በሚችሉበት ጉዳይ ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር መግባባት ላይ የተደረሰና መኖሪያዎችን እየገነቡ ያሉ ኩባንያዎች መኖራቸውም ነው የተገለጸው፡፡

በትዕግስት ስለሽ

You might also like
Comments
Loading...