Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ የብሪታንያ አምባሳደር ኪም ዳሮች ከሃላፊነታቸው ለቀቁ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 3 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የብሪታንያ አምባሳደር ኪም ዳሮች ከሃላፊነት መልቀቃቸውን አስታወቁ።

አምባሳደሩ በዛሬው እለት በስራቸው ለመቀጠል አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

በአሜሪካ ከሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ አምባሳደሩ የትራምፕን አስተዳደር “የማይታመንና አቅመ ቢስ” በሚል ገልጸውበታል የተባለ መረጃ ባለፈው እሁድ አፈትልኮ መውጣቱ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም አምባሳደሩ በእርሳቸው ላይ ያነጣጠረ ትችት ከትራምፕ ሲደርስባቸው ቆይቷል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕም አምባሳደሩን ጠንከር ባሉ የስድብ ቃላቶች ገልጸዋቸዋል ነው የተባለው።

አምባሳደሩም በዚህ እሰጥ አገባ መሃል ሆኘ ስራየን መቀጠል አልችልም በማለት ከሃላፊነት መነሳታቸውን ገልጸዋል።

በአምባሳደርነት ባገለገሉበት ዘመንም ሆነ ባለፉት ጥቂት ቀናት ተፈጥሮ በነበረው ከባድ ጊዜ ከጎናቸው ለነበሩም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይን ጨምሮ ተቀናቃኝ የሃገሪቱ ፓርቲዎችም ከአንጋፋው አምባሳደር ጎን መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል።

የሃገሪቱ ፖለቲከኞች አምባሳደሩን “ሃገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ” በሚልም አሞካሽተዋቸዋል።

ኪም ዳሮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህነት አማካሪነት ጀምሮ እስከ አምባሳደርነት ብሪታንያን ለ42 አመታት አገልግለዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አንድ አመት ቀደም ብሎም በአሜሪካ የብሪታንያ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ

You might also like
Comments
Loading...