Fana: At a Speed of Life!

በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ወላጆች በመኖሪያነት ካስመዘገቡት ቤታቸው ቀንሰው የሚሰጡበት አሰራር ተዘርግቷል

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 24 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች ወላጆች በመኖሪያነት ከተመዘገበው ቤታቸው ቀንሰው የሚሰጡበት አሰራር ተዘርግቶ ወደ ስራ ገብቷል።

አሰራሩ የመሸጫ ቦታዎችን እጥረት ለመቅረፍ በማሰብ የተተገበረ መሆኑን የፌደራል ከተሞች ስራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የመሸጫ ቦታ እጥረት ምርትና አገልግሎት ፈላጊዎችን እንዳይገናኙ በማድረግ የታሰበውን ያክል የስራ እድል እንዳይፈጠር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ለመቅረፍም ኤጀንሲው ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር አሰራሩ ይተገበር ዘንድ ስምምነት ላይ መድረሱንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈም ለረጅም ጊዜ በአንድ ሼድ የመቆየት፣ የመልካም አስተዳደርና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድም መንግስት የሚስተዋለውን ክፍተት በመቅረፍ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡም መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

በአፈወርቅ አለሙ

 

You might also like
Comments
Loading...