Fana: At a Speed of Life!

ሲጋራ ማጨስ በዓይናችን ላይ እስከ አይነስውርነት የሚያደርስ ጉዳት ያስከትላል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሲጋራ ማጨስ የሚያስከትለው ጉዳት ሲነሳ በብዛት በሳንባ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ነው ቀድሞ የሚመጣብን።

በርካቶች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም ሲጋራ ማጨስ በሳምባ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት እና ለካንሰር ተጋላጭነትን ከፍ ከማድረጉ በዘለለ በዓይን ላይ የጤና ችግር እንደሚያስከትል እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት።

ለአብነትም በጉዳዩ ዙሪያ 2 ሺህ ሰዎች ተጠይቀው 18 በመቶዎቹ ሲጋራን ማጨስ ለአይነ ስውርነት እንደሚዳርግ በትክክል እንደሚያውቁ የተናገሩ ሲሆን፥ 76 በመቶው ግን በዓይን ላይ ጉዳት ስለማድረሱ እንደማያውቁ ነው የተሰበሰበው መረጃ ያመለከተው።

የብሪታንያ ተመራማሪዎች ግን ከሰሞኑ ባወጡት አዲስ መረጃ ሲጋራን አዘውትሮ ማጨስ ሳምባ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጓዳኝ አይናችን ላይም እስከ አይነ-ስውርነት የሚዳርግ ከፍተኛ የጤና እክል ሊያስከትል እንደሚችል ነው ያስታወቁት።

እንደተመራማሪዎቹ ገለጻ ከሆነ ሲጋራን አዘውትረው የሚያጨሱ ሰዎች ከማያጨሱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ አጫሾች ለአይነ ስውርነት የመጋለጥ አድላቸው በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።

ምክንያቱ ደግሞ ከሲጋራ የሚወጣው ጭስ ዓይናችን ላይ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ስለሚያባብስ ነው ተብሏል።

የሲጋራ ጭስ መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎችን በውስጡ ያየዘ ነው ያሉ ሲሆን፥ ይህ ደግሞ አይናችን በቀላሉ ለጉዳት እንዲዳረግ በር ይከፍታል ሲሉም አመላክተዋል።

በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስ ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚከሰት እይታ ችግርን የበለጠ ያባብሳል የተባለ ሲሆን፥ ይህም ከአይናችን ሬቲና ጀርባ ያሉ የደም ቧንቧዎችን ከጥቅም ውጭ በማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

ይህንን ተከትሎም ተመራማሪዎች መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ አያይዘው ያስቀመጡ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው ሲጋጫ ማጨስ ማቆም እና በየጊዜው የአይናችንን ደህንነት ሁኔታ መከታተል ነው ብለዋል

ምንጭ፦ www.bbc.com

You might also like
Comments
Loading...