Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ 60 አዋጆችን በማጽደቅ 32 ውሳኔዎችን ማሳለፉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዓመቱ 60 አዋጆችንና 2 ደንቦችን በማጽደቅ 32 ውሳኔዎችን ማሳለፉ ተገለፀ።

የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የ2ዐ11 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀምን የገመገመ ሲሆን፥ በግምገማውም በበጀት አመቱ የታቀዱ ግቦችንና የተከናወኑ ተግባራትን አንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ በማተኮር ሰፊ ውይይት አድርጓል።

በዚህም በመላው ሀገሪቱ የተጀመረውን ሪፎርም ተከትሎ የፌዴራል መንግስት አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና አደረጃጀት ማሻሻያ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡

ቋሚ ኮሚቴዎችን በአዲስ መልክ በማደራጀት የተቋማቱን ሥልጣንና ተግባራት የሚመጥን ክትትልና ግመገማ በማድረግ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ 6ዐ አዋጆችንና 2 ደንቦችን ያፀደቀ ሲሆን 32 ውሳኔዎችን ማሳለፉም ተመልክቷል።

ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በጋራ በተሠጠው ሥልጣን መሠረትም 2 ውሳኔዎችን በጋራ ማስተላለፉን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የፓርላመንታዊ የአሠራር ስርዓትን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም በማጐልበት የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻሉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በዚህም ከሃገራት ጋር ያለውን ወዳጅነትና ትብብር የሚያጠናክሩ፣ የዜጐችን ዴሞክራሲና የመደራጀት መብት የሚያጐለብቱ፣ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ አንዲሠፍን የሚያደርጉ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጐልበት የሚያስችሉ አስተዋፆኦችን ሊያበረክቱ የሚችሉ ህጎችን ማውጣቱ
ተገልጿል።

ለመንግስት እቅድ አፈፃፀም ድጋፍ የሚያስገኝ የፓርላማ ዲፕሎማሲ የመፈፀም አቅምን ለማሳደግና የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የተሠራው ሥራ የሀገሪቱን የሪፎርም እንቅስቃሴ የሚያንፀባርቅ አንደነበረም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ1ዐዐ ቀን ወይም የአንድ ገፅ እቅድ እንዲሁም አመታዊ የተቋማት ዕቅዶችን በመገምገም ግብረ መልሶችን መስጠት ችለዋል ነው የተባለው፡፡

ተቁማት ከሚያቀርቡት እቅድ በመነሳትም ጉድሎቶችን በመለየት ማስተካከያ እንዲያደርጉ አቅጣጫ በማመላከት እና ተቀባይነት የሌላቸው አቅዶችን ውድቅ በማድረግ የሚፈፀምና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያርግ መልኩ አንዲያዘጋጁ ተደርጓል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚንስትሮች የጥያቄ ጊዜ በአቅድ የተያዘ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተገኙበት አንድ የጥያቄ ጊዜ ውጪ አለመደረጉ እንደክፍተት በሪፖርቱ የተካተተ ሲሆን፥ በቀጣይ ሊታረም እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አፈፃፀም መዘግየትና የጥራት ችግር፣ የፓርኮችና ቱሪዝም መዳረሻዎች ጉዳት መድረስ፣ የብርዕ፣የጥራጥሬ፣ የቅባትና የቅመማቅመም ሰብሎች ምርታማነትን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ዝቅተኛ መሆን ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው ተብሏል፡፡

እንዲሁም በአንደንድ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት በፀጥታ ችግር መስተጓጐሉ በምክር ቤቱ አባላት ክትትልና ቁጥጥር ከተለዩ ችግሮች መካከል ይገኛል፡፡

የምርጫ ክልል ግንኙነት አሠራርን በማሻሻል ለህዝቡ ወቅታዊ የሆነ መረጃ አና ምላሽ አሠጣጥን በማሳደግ የህዝብ ውክልና አፈፃፀም ሥራ ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ቢሆንም ቀሪ ተግባራት እንዳለ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ሪፖርቱ ከተደመጠ በኃላ በተጠናቀቀው በጀት አመት የምክር ቤት አባላት የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለ፣ ጥገና ፍትሃዊ አለመሆን፣ የህክምና አገልግሎት አሠጣጥ ቀልጣፍ አለመሆን ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ አለመሆን እንዲሁም የመስክ ሥራ ለመሥራት የሚከፈለው የውሎ አበል በቂ አለመሆን ከአባላት የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች ሃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ከአባላት አገልግሎት አሠጣጥ ጋር የተነሱ ችግሮች በ2ዐ12 ዓ.ም ለመቅረፍም ከስምምነት ላይ ተደርሶ የበጀት ዓመቱ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መጠናቀቁን ከምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like
Comments
Loading...