Fana: At a Speed of Life!

አለም አቀፉ የልማት ማህበር (አይዳ) ለኢትዮጵያ ባደረጋቸው ድጋፎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 11 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም አቀፉ የልማት ማህበር (አይዳ) ለኢትዮጵያ ባደረጋቸው ድጋፎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

የአለም አቀፉ የልማት ማህበር ከ2021 እስከ 2023 ለታዳጊ ሀገራት ለሚያደርገው ድጋፍ ከለጋሽ ሀገራት ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችለውን ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአለም ባንክ አካል የሆነው አይዳ በተለይም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራም ያደረጋቸው ድጋፎች አመርቂ ውጤት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የአለም ባንክ በአለም አቀፉ የልማት ትብብር ወይም አይዳ በኩል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው 75 ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

የእርሻ፣ እንሰሳት ሀብት ልማት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ እና ልማት፣ የከተማ እና የመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን፣የገጠርና የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች በአይዳ ድጋፍ ተከናውነዋል።

ከዚህ ባለፈም አይዳ ባለፉት አመታት በትምህርት፣ ጤና፣ ማህበራዊ ዋስትና፣ የፆታ እኩልነት፣ መልካም አስተዳደር ግንባታ እና ሌሎች ዘርፎች ድጋፍ አድርጓል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የመንገድ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችም በአይዳ ድጋፍ እና የብድር አቅርቦት መካሄዳቸውን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።

ሀገሪቱ በ2010 እና 2011 ብቻም ከአይዳ ከ5 ቢሊየን ዶላር ያላነሰ የልማት ፋይናንስ በዕርዳታ እና በብድር መልክ ድጋፍ አግኝታለች።

በዚህም በተለያዩ ዘርፎች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መከናወናቸውን ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያነሱት።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፥የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ ልማት ትልቁን እገዛ የሚያደርግ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

ባንኩ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች እያደረገ ካለው ድጋፍ ባሻገር በዚህ አመት የበጀት ድጋፍ ማድረጉን እና የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች እያገዘ መሆኑንም አንስተዋል።

የአለም ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክሪስትሊና ጎዮርጌቫም ፥ባንኩ በአይዳ በኩል ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ከአይዳ የተደረገላትን ድጋፍ በአግባቡ በማዋሏና የጀመረቻቸው የሪፎርም ስራዎች ስኬታማ ይሆናሉ ተብሎ በመታመኑ የማህበሩ የ2019 ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ምክንያት መሆኑንም አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአለም ባንክ ድጋፍ ከ13 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ መሆኑ ተገልጿል።

ይህም ግዙፍ አጋርነት ነው ያሉት የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ፥ ባንኩ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ስብሰባም 80 ቢሊየን ዶላር ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው ያብራሩት።

አይዳ ሊሰበስበው ካሰበው 80 ቢሊየን ዶላር ውስጥ የአፍሪካ ቀንድ እና የሰሃራ በታች ሀገራት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ።

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር እና ለቀጠናዊ ትብብር ከሚደረጉ ድጋፎች ከአይዳ የሚደረግላት ድጋፍ ከፍ ይላል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like
Comments
Loading...