Fana: At a Speed of Life!

በሀገሪቱ በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 614 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቱ በሚገኙ አራት ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ 614 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬተር ዶክተር በየነ ሞገስ የበሽታውን ስርጭት አስመልክተው በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር በየነ በመግለጫቸው የኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ በኦሮሚያ፣በአማራ፣ በትግራይ፣በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መከሰቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 614 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ ተይዘዋል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።

በዚህ መሰረትም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን አምስት ወረዳዎች እንዲሁም በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰንዳፋ ከተማ በአጠቃላይ 294 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ 198 የሚሆኑ ሰዎች በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሲሆን፥14 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው አልፏል።

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል 33 ሰዎች እንዲሁም በትግራይ ክልል ደግሞ 18 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ነው ያሉት ዶክተር በየነ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ9 ክፍለ ከተሞች 70 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ በሽታ መያዛቸው በመግለጫው ተመላክቷል።

በተጨማሪም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንድ ሰው በበሽታው መያዙን በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤትማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉ ዶክተር በየነ።

በሽታውን ለመቆጣጠርም ናሙናዎችን በጥናት በመለየትና በላቦራቶሪ በማረጋገጥ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመድሃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦትእየተሰራጨ መሆኑን ዶክተር በየነ ገልፀዋል።

ከዚህ ባለፈም ከሃይማኖት ተቋማት ጋር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ትምህረት ቢሮ ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ለመጀመር ስምምነት ላይ መደረሱን ተቁመዋል።

ከነገው ዕለት ጀምሮም በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በሁለት ዙር በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።

ህብረተሰቡም በክረምት ወራት በወረርሽኝ መልክ ከሚከሰቱ በሽታችዎች እራሱን ለመከላከል በቂ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የኢቦላ ወረርሽ በሁለት የአፍሪካ ሀገራት መከሰቱን ተከትሎ በሽታው ወደ ሀገሪቱ እንዳይገባ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ዶክተር በየነ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረተም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተጓዦችን የሙቀት መጠን ልየታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአውሮፕላን ማረፊያው በበሽታው የተያዙ መንገደኞች ቢያጋጥሙ ለይቶ ለማከም የሚያስችል ቦታ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ዶክተር በየነ፥ ከዚህ በተጨማሪም በቦሌ ጨፌ የኢቦላ ለይቶ ማከሚያ ማዕከል መዘጋጀቱን አንስተዋል።

በሲሳይ ጌትነት

You might also like
Comments
Loading...