Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ምክክር እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት ነጻና ገለልተኛ ተቋም ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ምክክር እየተደረገ ነው።

ምክር ቤቱ በዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ እንዲሁም በረቂቅ የጋራ ምክር ቤቱ የቃል ኪዳን ሰነድ ማሻሻያና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

የምክር ቤቱ የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቡድን ረቂቅ የቃል ኪዳን ሰነዱን አቅርቧል።

በዚሁ መሰረት የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ሄኖክ አክሊሉ÷ በምክር ቤቱ አባል የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብያኔን የተመለከተ ማሻሻያ አቅርበዋል።

በዚህም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር የምክር ቤቱ አባል የሚሆኑበትን ሁኔታ በማስቀረት ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ፓርቲዎች ብቻ አባል ይሆናሉ።

የቃል ኪዳን ሰነድ ማሻሻያው ምክር ቤቱ ነጻነቱን በጠበቀ መልኩ ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው ያደርጋል ብለዋል።

ለዚህም ምክር ቤቱ እንደ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት እንዲመዘገብ፣ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በአዋጅ ተቋቁሞ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለምርጫ ቦርድ እንዲሆን  ለውይይት ቀርቧል።

የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ ‘ይሻላል’ ያሉትን ሃሳብ እያቀረቡ ከተወያዩ በኋላ፣ ጉዳዩ ዳግም ዝርዝር ጥናት ተደርጎበት እንዲቀርብ ከውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ገሚሱ የምክር ቤት አባላት የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት የተባለው ጉዳይ ፈጽሞ የማያስኬድ መሆኑንና በሕገ መንግሥቱ መሰረት በአዋጅ ማደራጀቱ የተሻለ መሆኑን ገልፀዋል።

የተቀሩት ደግሞ ሁለቱንም አማራጮች በመተው ምክር ቤቱ ለምርጫ ቦርድ ተጠሪ ሆኖ ይደራጅ  ብለዋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በሥሩ የሚገኙ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚደራጁበትንና አስተባባሪዎች የሚመደቡበትን ሂደት የሚያሻሻል ውሳኔም አጽድቀዋል።

በዚሁ መሰረት ቋሚ ኮሚቴዎች በምክር ቤቱ አባላት ከተደራጁ በኋላ አስተባባሪዎቹም በምክር ቤቱ አማካኝነት ‘ይመደባሉ፤ ይነሳሉ’ በሚለው የአሰራር ሂደት ላይ ተስማምተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ÷ ምክር ቤቱ መጪው ምርጫ ሠላማዊ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ አገሪቱ የተሳካ ምርጫ እንድታካሂድ ፓርቲዎችን የማቀራረብና ከምርጫ ቦርድ ጋር በቅርበት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን የሚያቋቁም ሲሆን የክልል አደረጃጀትም እንደሚዘረጋ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.