Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ሩሲያ የስነ ህይወታዊ አካላት የምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ሩሲያ የስነ ህይወታዊ አካላት የምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ ሊቋቋም ነው።

የሩሲያ የሳይንስ አካዳሚ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኢትዮ ሩሲያ የስነ ህይወታዊ አካላት የምርምር ማዕከልን ለማቋቋም እቅድ ይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተነጋግረው በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሰረትም ማዕከሉ ወደ ትግበራ ይገባል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ኢቭጀኒ ተረኪህን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና የሩሲያ መንግስታት የጋራ ኮሚሽን በኢትዮጵያ በኩል ሰብሳቢ በመሆናቸው የጋራ ኮሚሽኑ ስብሰባ በሚካሄድበት ቀንና በሚቀርቡ አጀንዳዎች ዙሪያ መክረዋል።

ከዚህ ባለፈም የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለህክምናና ለሃይል መጠቀም እንዲቻል በተቀመጠው ፍኖታ ካርታ ትግበራ ዙሪያ መምከራቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከዚህ በተጨማሪም የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በማዕድን ፍለጋ መስክ (በወርቅና ታንታለም) መሰማራት በሚችሉበት አግባብ ዙሪያም ውይይት አድርገዋል።

You might also like
Comments
Loading...