Fana: At a Speed of Life!

የባንኮች አዳዲስ ብድር የማበደርና የመሰብሰብ አቅም ከፍ ማለቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የባንኮች አዳዲስ ብድር የማበደርና የመሰብሰብ አቅም ከፍ ማለቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

በባንኩ የገንዘብና ፋይናንስ ትንተና ዳሬክተር አቶ ሙሉነህ አያሌው ከፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥በብሄራዊ ባንክ ቀደም ሲል የብድር ጣሪያ ከ16 ነጥብ 5 በመቶ በላይ እንዳያድግ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱን ተከትሎ የባንኮች አዳዲስ ብድር የማበደርና የመሰብሰብ አቅም ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
 
በዚህ መሰረትም ባንኮቹ በዘንድሮ ዓመት ከ160 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ አዳዲስ ብድር ማበደር የቻሉ ሲሆን፥ ከ108 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ቀድመው ያበደሩትን ገንዘብ መሰብሰብ ችለዋል ነው ያሉት አቶ ሙሉነህ።

ባንኮቹ ባለፈው ዓመት ካበደሩት 110 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ጋር ሲነጻጸርም የዘንድሮው ከፍ ማለቱ ነው የተገለፀው።

የአባይ ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ የኋላሸት ገሰሰ  በአሁን ወቅት ባንኮች የቁጠባ ክምችታቸው ማደጉን ይናገራሉ።

እንደ አባይ ባንክም አዳዲስ ብድሮችን በማበደር ረገድ ከአምናው 30 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

በብሄራዊ ባንክ ቀደም ሲል የብድር ጣሪያ ከ16 ነጥብ 5 በመቶ በላይ እንዳያደግ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱን ደግሞ ገበያው በሚፈልገው ልክ ለማበደር ማስቻሉን አንስተዋል።

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ስራ አስኪያጅ እና ኢኮኖሚስት ደቻሳ ፋንታ በበኩላቸው፥ ብሄራዊ ባንክ ያደረገው የብድር ጣሪያ ገደብ ነጻ መሆን ባንኮቹ የማበደር አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ያስችላል ባይ ናቸው።

በባንኮቹ የሚሰጠው አዳዲስ የብድር መጠን ከፍ ማለት ደግሞ ተበዳሪዎች ለመንግስት  የሚከፍሉት ገቢ እና ግብር እንዲሁም የስራ አድል አንዲጨምር በማሰቻል በኢኮኖሚው ላይ ከፍ ያለ አሰተዋፅዖ ይኖረዋል ነው ያሉት።

ባንኮቹ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ 27 ከመቶ የማበደር ግዴታቸውንም ከዚህ በተሻለ መወጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ 19 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብድር ከባንኮቹ አግኝቷል።

ብሄራዊ ባንክም ከባንኮቹ የሚያገኘውን ብድር ለማዕከላዊ መንግስት ለልማት ብድር የሚሰጥ ሲሆን ፥ ይህም የባንኮቹ የማበደር አቅም 22 ከመቶ በላይ ማደጉን የሚያመላክት መሆኑን አቶ ሙሉነህ ገልፀዋል።

ከባለፈው ዓመት ጋር ብሄራዊ ባንክ ከባንኮቹ ከተበደረው 16 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ጋር ሲነጻጸር የዚህ በጀት ዓመቱ ማደጉን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የብድር ጣሪያ ከ16 ነጥብ 5 በመቶ በላይ እንዳያደግ ጥሎት የነበረው ገደብ ማንሳቱ ይታወሳል።

ሆኖም ባንኮቹ አዳዲስ ብድሮችን የመስጠት አቅማቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ ከቀድመው ያበደሩትን ብደር የመሰብሰብ አቅማቸወም አድጋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ108 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ቀድመው ያበደሩትን የሰበሰቡ ሲሆን፥ ባለፈው ዓመት ከሰበሰቡት 75 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ጋር ሲነጻጸር የመሰብሰበ አቅማቸው መጨመሩን ያሳያል።

ባንኮቹ ከሰበሰቡት ብድር ውስጥ ከግብርና ዘረፍ አምና በተመሳሳይ ወቅት 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፥ በዘንድሮ ደግሞ  7 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ብደር መሰብሰባቸውን አቶ ሙሉነህ አንስተዋል።

በተመሳሳይ  ከኢንዱስትሪ ዘርፍ አምና 14 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሰበሰቡ ሲሆን፥ ዘድሮ ደግሞ 15 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መሰበሰብ መቻላቸው ተገልጻል።

ከሀገር ውስጥ ንግድም በተመሳሳይ በዘንድሮ ባንኮቹ ያበደሩትን 17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፥ አምና በተመሳሳይ ወቅት 15 ነጥብ 8 መሰብሰቡ ይታወሳል ።

በዚህም ከግብርናው ከሰበሰቡት ብድር 27 ነጥብ 5 ከመቶ ፣ ከሀገር ወስጥ ንግድ 12 ነጥብ 1 በመቶ ከኢንዱስትሪ ዘረፍ ደግሞ 22ነጥብ 1 በመቶ የመሰብሰብ ዕድገት አሳይተዋል።

እንደ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ስራ አስኪያጅ ደቻሳ ፋንታ ገለጻ ግን ባንኩ ቀድሞ ያበደረውን የመሰብሰብ አቅሙ ከአምና የተሻለ ቢሆንም በምዕራብ እና ደቡብ አካባቢ ላይ ግን ባንኮች ብድራቸውን የመሰብሰብ አቅማቸው በነበረው  አለመረጋጋት ችግር ምክንያት አዝጋሚ እንደ ነበር አንስተዋል።

ባንኮቹ አዳዲስ ብደር ከመስጠትና ቀድመው ያበደሩትን ብድር ከመሰብስብ አንጻር አቅማቸው አድጓል ከመባሉ በተጨማሪ፥ ንግድ ባንክን ሳይጨምር ሁሉም ባንኮች በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ150 ቢሊየን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ብር ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሲሆን፥ይህም ባንኮቹን የሚጠቀሙ ደንበኞች የቁጠባ ልምዳቸው መዳበሩን የሚያመላከት መሆኑ ተመላክቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like
Comments
Loading...