Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን የፖለቲካ ሀይሎች ውይይት ውጤታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ ድጋፏን ትቀጥላለች- አቶ ገዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሱዳን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ናዲያ ሞሃመድ ከይር ተወያዩ፡፡

ሚኒስትሩ በሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ምክክር በጥሩ ሁኔታ በመቀጠሉ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሱዳን ዘላቂ ሰላም ትኩረት እንደምትሰጥና በመካሄድ ያለው የፖለቲካ ውይይት ገንቢ ውጤት እንዲያስመዘግብ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥልም ገልፀዋል፡፡

አምባሳደር ናዲያ በበኩላቸው የፖለቲካ ምክክሩ በመግባባትና በስምምነት መንፈስ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ይህም አስታራቂ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ሱዳን በቀጣናው፣ በአህጉራዊና በአለም አቀፍ መድረኮች ለምታደርጋቸው ግንኙነቶች ኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል አምባሳደሯ መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ካትሪን ምዋንጊ ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
 
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራና ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ግንኙነት እንደላቸው ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ከኬንያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።
You might also like
Comments
Loading...