Fana: At a Speed of Life!

 ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ የማስ ስፖርት በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ ከ50   ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ የማስ ስፖርት የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ ከተማ የማስ ስፖርትን በይፋ ለማስጀመር በተዘጋጀ መድረክ ላይ ፥ከዘርፉ ከተውጣጡ 33 ፌደሬሽን ፕሬዚዳንቶች እና 3 አሶሴሽን ስራ አስፈፃሚዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይቱም የማስ ስፖርት ፕሮግራም በዋነኛነት ህብረተሰቡ በሚማርበት ፣ በሚሰራበት እና በሚዝናናበት አከባቢ ጤና ተኮር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

እንዱሁም  ከዘረኝነት አስተሳሰብ የፀዳ ፣ በመቻቻል በመግባባትና በመከባበር መልካም እሴቶችን የሚያከብር፣ ከአደገኛ ሱሶች የራቀ ህብረተሰብ መፍጠርን አላማ ያደረገ ነው ተብሏል።

በዚህም መሸረጽም 50 ሺህ  የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የሚሆኑበት መርሃ-ግብር የፊታችን እሁድ በመስቀል አደባባይ የሚካሄድ መሆኑን የከንቲባ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በኢንጂነር ታከለ ኡማ አነሳሽነት በሚካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ሚኒስቴሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የአዲስ አበባ ከተማ የካቢኔ አባላት፣ አርቲስቶች፣ የስፖርት ማህበራት፣ የእግር ኳስ ደጋፊ ማህበራት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተካፋይ ይሆናሉ፡፡

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከስፖርት ማህበራት ጋር በመሆን የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ እና በተግባር ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ እና ስፖርት ዘረኝነትንና ቂምን በማስወገድ ፍቅር ፣ አንድነትንና መቻቻልን የሚያመጣ አንዱ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዚህ አይነቱ መርሃ-ግብር ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የስፖርቱ ዘርፍ እንዲያድግ የሚረዳ በመሆኑ በተከታታይነት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡

 

You might also like
Comments
Loading...