Fana: At a Speed of Life!

በ9 ወራት ወደ መዲናዋ ሊገቡ የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ሽጉጦችና በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

አዲስ አባባ፣ ግንቦት 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 9 ወራት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሊገቡ የነበሩ 10 ሺህ ሽጉጦና በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጠ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት አብራርተዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፥ ባለፉት 9 ወራት በተለያዩ መንገዶች ወደ ከተማዋ ሊገቡ የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ሽጉጦች፣ 30 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች፣ 4 መትረየስ እና ከ19 ሺህ በላይ ጥይቶች ከህገ ወጦች ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።

በከተማዋ ሁከትና ረብሻ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ሀይሎች ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በተጨማሪ ከ180 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና የልዩ ልዩ ሀገራት ገንዘቦች በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር እንደተያዘም ጨምረው ገልፀዋል።

ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃጸር ለህብረተሰቡ ስጋት የሆኑ ከባድ ወንጀሎችን በቁጥር 825 መቀነሱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፥ የከተመዋን ነዋሪዎች ይበልጥ በማስተባበር ህገ ወጦችን በመከላከል የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር ጌቱ አክለውም፥ በከተመዋ በቡድን ተደራጅተው ልዩ ልዩ የዘረፋ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ ከ1 ሺህ 680 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።

ከወንጀለኞች ጋርም ከ100 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር፣ ከ200 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር እና የልዩ ልዩ ሀገራት ገንዘቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

የመንገድ ትራፊክ አደጋን መከላከል የሚቻለው አሽከርካሪዎችና እግረኞች የመንገድ ደንብና ህግጋትን አክብረው መንቀሳቀስ ሲገባቸው ነው ያሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል ብለዋል።

አዲስ አበባ በርካታ የፖለቲካና የንግድ መናሃሪያ እንደመሆኗ መጠን ነዋሪው ከአሁን በፊት እንዲሚያደርገው ሁሉ ለፖሊስ መረጃዎችን እየሰጠ መሆኑ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፥ በቀጣይ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን በመሆን የከተማዋን ሠላምና ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በትጋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ህብረተሰቡም ሆነ የሚዲያ ባለሙያዎች ከፖሊስ ጎን በመሆን መረጃዎችን በመስጠትና በመተባበር የወንጀልና ትራፊክ አደጋን የመከላከል ስራን እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like
Comments
Loading...