Fana: At a Speed of Life!

በግል ይሰጥ የነበረው የቤት ለቤት የህክምና አግልግሎት በመንግስት ደረጃ መሰጠት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በግል ይሰጥ የነበረው የቤት ለቤት የህክምና አግልግሎት በመንግስት ደረጃ በተመረጡ 10 ከተሞች መሰጠት መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት በመንግስት ወደ ሙከራ ትግበራ መግባቱን የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ አገልግሎቱን በተመረጡ 10 ከተሞች መንግስት በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ነው ሚኒስትሩ የሚናገሩት፡፡

አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጅማና ድሬዳዋ ከተሞች አገልግሎቱ በሙከራ ደረጃ ትግበራ የተጀመረባቸው ከተሞች ናቸው ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ በተለይም ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ስኳርና ደም ግፊት ያሉ በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከልና የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ህሙማኑ ህክምናውን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሙከራ ትግበራው ሂደትም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

አገልግሎቱ በሌሎች ሀገራት ተግባራዊ የሚደረግና የጤናውን ዘርፍ ያሳደገ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም የህክምና አገለግሎቶች የሚሰጡበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አገልግሎቱን የሚሰጡት ባለሙያዎችም የተለያየ ደረጃ ያላቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ይህ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችና የገቢ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ከዚህ ባለፈም መንግስት በግሉ ዘርፍ በዚህ አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁን

You might also like
Comments
Loading...