Fana: At a Speed of Life!

በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አቅራቢያ በሁለት የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት ተሰነዘረ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 5፣2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ፉጃራህ ወደብ በሁለት ነዳጅ የጫኑ የሳዑዲ ዓረቢያ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገለፀ።

በትናንትናው ዕለት በፉጃራህ ወደብ ማንነታቸው ባልታወቁ ሃይሎች በተሰነዘረ ጥቃት በሁለት ነዳጅ በጫኑ  የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጉዳት መድረሱን የሀገሪቱ የኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢነርጂ ሚኒስትሩ ካህሊድ አል ፋሊህ ጉዳዩን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በመርከቦቹ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በቀጠናው የሚከናወነውን ነዳጅ ዘይትን በባህር ላይ የማስተላለፍ ሂደታ ለማስተጓጎል የተሸረበ ሴራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ነዳጅ ዘይትን የሚያቀርቡ ሀገራትንና ሸማቾችን በቀጠናው የደህንነት ስጋት እንዳለ ለማስመሰል የታቀደ አሻጥር መሆኑን አንስተዋል ።

በጥቃቱ ምንም አይነት ኪሳራ አለመድረሱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ በመርከቦች መዋቅር ላይ ግን ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል ።

ጥቃት ፈፃሚዎችን ለማወቅም  ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በቀጠናው ያለውን ሰላማዊ የባህር ላይ ጉዞ የሚያስተጓጉሉ አካላትን ለመከላከል የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ ፦presstv.com

You might also like
Comments
Loading...