Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸው አካባቢዎች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን አካባቢዎች ይፋ አደረገ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ ምክር ቤት በክልሉና ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ በማተኮር ያካሄደውን ስብሰባ አጠናቋል።

በቅርብ ጊዜያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መከሠቱና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እዲሁም በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎም የክልሉ መንግሥት ከፌደራል የፀጥታ አካላት እና ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት ግጭቶችን ለማስቆም፣ ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ፀጥታ ለማረጋገጥ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስና በግጭቱ የተሳተፉ አካላትን ለህግ በማቅረብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ በትናትናው ዕለት በመተከል ዞን በዳንጉር፣ በማንዱራ፣ በፓዊና በድባጤ ወረዳዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች መሠረታዊ መነሻ ምክንያቶች፣ ግጭቶቹን ለማስቆም በተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች፣ እንዲሁም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡

በውሳኔውም ግጭት በተከሰተባቸውም ሆነ በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ድምፅ አልባ መሣሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ ተከልክሏል፡፡

በልዩ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጭ የክልሉ ሚሊሻ አባላትም ሆኑ የቀበሌ ታጣቂዎች ህጋዊም ይሁን ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ መከልከሉን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከዚህ ባለፈም በተደራጀ መንገድም ሆነ በተናጠል ወደ አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጥቃት ለመፈፀም የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ፍፁም ህገ-ወጥ፣ በየትኛውም አካላት ተቀባይነት የሌለው እና የተወገዘ ከመሆኑም ባለፈ በልዩ ሁኔታ በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑንም ገልጿል።

እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌደራል ፖሊስ ውጭ በአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ በ5 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስንም ከልክሏል።

የፀጥታ ምክር ቤቱ እነዚህን ውሳኔዎች ለጋራ ሠላምና ፀጥታ እጅግ በጣም ወሳኝና መሠረታዊ መሆናቸውን በጥልቀት በመገንዘብ የመተከል ዞንና በተጠቀሱት አራት ወረዳዎች የተዋቀሩ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቶች በጥብቅ እንዲከታተሉና እንዲያስፈፅሙም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

You might also like
Comments
Loading...