Fana: At a Speed of Life!

በመካከለኛው ምስራቅ ታዋቂ የቡና ውጤቶች አምራች የሆነው ማቱክ ኩባንያ ፕሬዚዳንት በሰኔ ወር ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 28 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ ታዋቂ የቡና ውጤቶች አምራች የሆነው ማቱክ ኩባንያ ኢትዮጵያ በቡና ኢንቨስትመንት ያላትን አማራጭ በማየት መዋእለ ንዋዩን ለማፍሰስ የፊታችን ሰኔ ወር ፕሬዚዳንቱን ይልካል።

ማቱክ ቡናን በተለያየ መልኩ አቀነባበሮ ለዓለም ገበያ የሚያቀረብ ኩባንያ ሲሆን፥ በተለይም በባህረ ሰላጤው ሀገራት በርከት ያሉ ሱቆች አሉት።

ኩባንያው ከኢትዮጵያ ቡና የሚገዛ ሲሆን፥ መጠኑ ግን በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን ተከትሎ ነው በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ኩባንያውን የጎበኙት።

በዋናነትም ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ቡናን በተለያየ መልኩ አቀነባበሮ ወደ ውጭ እንዲልክ በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ ማስቻል ነው።

አምባሳደሩ በጉብኝታቸው ወቅትም በኢትዮጵያ ስላለው የቡና ምርት ዓይነትና መጠን ገለፃ ሰጥተዋል።

የማቱክ ኩባንያ ፕሬዚዳንት ሰሚራ ማቱክ በገለፃው መደሰታቸውን በመግለፅ የበለጠ የኢትዮጵያን ቡና መግዛት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር በቀጣይ ሰኔ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ አረጋግጠዋል።

በቆይታቸውም የቡና አምራች አካባቢዎችን በመጎብኘት አርሶ በአደሮችን አግኝተው እንደሚያነጋግሩ ነው ያመለከቱት።

ሁለቱም ወገኖች ኩባንያው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲኖረው ለማድረግ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው የተስማሙት።

ኢንቨስትመንቱ ኢትዮጵያ ቡናን በሀገር ውስጥ አቀነባብራ ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ ከማስቻል ባለፈ የስራ እድልን የሚፈጥር እና አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል ነው ተብሎ ታምኖበታል።

ፕሬዚዳንቷ በሰኔ ወር በሚያደርጉት የኢትዮጵያ ጉብኝት ወቅትም ኢንቨስትመንቱን ወደ ተግባር የሚቀይር ስምምነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

በአንዱዓለም ሽመልስ

You might also like
Comments
Loading...