Fana: At a Speed of Life!

ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም ለምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም ለምታደርገው ጥረት የራሱን አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ተገለፀ።

በአዲስ አበባ ዩቨርሲቲ በአገር ልማት ጥናት ኮሌጅ ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ልማት ጉዳዮች መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር በላይ ስማኔ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፕሮጀክቱ ሶስት ዋና ዋና ጠቀሜታዎችን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ቀዳሚው አየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ረገድ ያለውን ፋይዳ ነው ያሉት ዶክተር በላይ፥ የአከባቢ ብክለትን በመከላከል ረገድም የአዲስ አበባን ወንዞች ገፅታ በመቀየር ረገድ የጎላ ድርሻ ይወጣል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ ከእነዚህ ባለፈ ሌላም ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ አለው ያሉ ሲሆን፥ ይህም በፕሮጀክቱ ስራ ወቅት እና ከተጠናቀቀ በኋላ በማለት ይከፍሉታል።

ቀዳሚው የፕሮጀክቱ ስራ ሲሰራ የሚፈጥረው የስራ እድል አሁን ላይ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር በተወሰነ መንገድ የሚያቃልል ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በሗላ የሚፈጥረውን ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ በራሱ በሁለት መንገድ ከፍለውታል።

ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ከአለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፖሊሲዎች እና ስምምነቶች ጋር የሚተሳሰር ነው ።

ለአብነት ያህል ከአለም አቀፍ ስምምነቶች እና ግቦች አኳያ ሲታይ ኢትዮዽያ ያፀደቀቸው በ2015 በጎርጎሮሳዊያኑ የተፈረመውን የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እና የዘላቂ  ልማት ማሳኪያ ግቦችን ከመተግበር አኳያ የየራሱ አስተዋፅኦ ያለው ነው።

ከ17ቱ የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል 11ኛው ግብ ለኗሪዎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን መፍጠር የሚል ሲሆን፥ የሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ደግሞ ትልቁ ግቡ ይህ ነው።

ዶክተር በላይ ስማኔ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከሀገራዊ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ጋርም የሚጣጣም ነው ይላሉ።

በእርግጥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተለያዩ ሀገራትም የእኔ የሚሉትን ፕሮጀክት ይፋ እያደረጉ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።

ጥያቄው ይህ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት የታሰበውን ዓላማ ያሳካ ዘንድ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለው ነው።

በስላባት ማናዬ

You might also like
Comments
Loading...