Fana: At a Speed of Life!

ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ለከተማዋ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል – ወጣቶች

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ለከተማዋ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠሪያ በመሆኑ ባለሀብቶች ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የመዲናዋ ወጣቶች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎችን እና መናፈሻዎችን የሚያለማውን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የተዘጋጀው የሸገር ገበታ መርሀ ግብር ከቀናት በኋላ ይካሄዳል።

እስከ አሁን ከ200 በላይ ተቋማትና ግለሰቦች በገንዘብና በተለያየ ደረጃ አስተዋጽዖ ለማበርከት ፍላጎት ማሳየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን በእውቀት በጉልበትና በገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ለመሳተፍ በተዘጋጀው ፕሮጀክት የከተማዋ ወጣቶች ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

ወጣቶቹ እንደሚሉት ከተማዋን ለሁለት ከፍለው የሚፈሱ ወንዞችን በማልማት ጽዱና ለመናፈሻነት የሚሆን ቦታ መስራት ይገባል።

የከተማዋን ወጣቶች ከሱስ ቤቶች በማራቅ እና በመናፈሻዎቹ እንዲያሳልፉ በማድረግ የመዝናኛነት ሚናም ይጫወታሉም ነው ያሉት ወጣቶቹ።

ከሰሜን አዲስ አበባ ከእንጦጦ ተራራ ስር ተነስቶ አቃቂ ወንዝ የሚዘልቀው 56 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍነው ይህ ፕሮጀክት፥ ለጤና አደገኛ በሆነው ጠረናቸው የሚታወቁትን ወንዞች በንጽህናቸው ተጠግቶ ለማረፍ የሚያጓጉ ለጎብኚዎችም መስህብነት እድልን የሚሰጥ እንደሚሆን ወጣቶቹ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በግንባታ ሂደትና ሲጠናቀቅም በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ እድል በመፍጠር ይጠቅማል በተባለለት ፕሮጀክት ላይ ለመዲናዋ ስራ አጥ ወጣቶች በረከት ይዞ እንደሚመጣም ያነሳሉ።

ባለሃብቱም በዚህ ታሪካዊ የመዲናዋን የማስዋብ መርሃ ግብር በመሳተፍ ለጎብኚዎች የተመቸች ከተማ ሊያደርጋት ይገባል ነው ያሉት።

ሸገርን የሚያስውበው ፕሮጀክት በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ታስባል።

በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጭነት ይፋ የሆነው ፕሮጀክት እንዲሳካ የተዘጋጀው የሸገር ገበታ ግንቦት 11 ቀን 2011 ለመካፈል መቀመጫ በ5 ሚሊየን ብር የገዙ አካላት ቤተ መንግስት የሚገኙ ሲሆን ምሽት ላይም በእራት ግብዣ ስነ ስርዓቱ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል።

 

በኃይለየሱስ መኮንን

You might also like
Comments
Loading...