Fana: At a Speed of Life!

ስካይ ዌይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ የኬብል ትራንስፖርት መዘርጋት የሚያስችለውን ሃሳብ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ስካይ ዌይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተሰኘው ኩባንያ በኢትዮጵያ የኬብል ትራንስፖርት መዘርጋት የሚያስችለውን ሃሳብ አቀረበ።

ኩባንያው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኢትዮጵያ የኬብል ትራንስፖርትን መዘርጋት የሚያስችለውን ሃሳብ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር አቅርቧል።

የኬብል ትራንስፖርት በከተሞች አካባቢ የሚስተዋለውን መጨናነቅ በመቀነስ ሰፊ ቦታ መቆጠብ እንደሚያስችል ኩባንያው ሃሳቡን ባቀረበበት ወቅት ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በመደበኛ ትራንስፖርት ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን በማገናኘት፥ ለትራንፖርት የሚወጣውን የሰው ጉልበትና ገንዘብ ለመቀነስ ያስችላልም ነው ያለው።

የቴክኖሎጅው መተግበር አስቸጋሪ የሆኑ ተራራማ ስፍራዎችን ለመድረስና የቢዝነስ ማዕከላትን ከአየር መንገድ ጋር ለማገናኘት እንዲሁም ሸቀጦችን በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ያግዛልም ነው ያለው ኩባንያው።

ከፕሮጀክቱ ትግበራ ጋር በተያያዘም ኩባንያው ፕሮጀክቱን ከግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን የማከናወን እቅድ እንዳለውም ሃሳቡን ባቀረበበት ወቅት አስታውቋል።

ከፕሮጀክቱ ወጪ ጋር በተያያዘ ከተሳፋሪዎች ጣቢያና መሰል የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ውጭ፥ አንድ ኪሎ ሜትር ፈጣን የኬብል ትራንስፖርት መስመር ለመዘርጋት እስከ 3 ሚሊየን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅም ገልጿል።

ስካይ ዌይ ኢንቨስትመንት ዋና መቀመጫውን ቤላሩስ ያደረገ በኬብል ትራንስፖርትና መሰል የቴክኖሎጅ ዘርፎች የተሰማራ ኩባንያ ነው።

በኢትዮጵያ ለመተግበር የታሰበው ፕሮጀክትም መቀመጫውን ኢትዮጵያ ባደረገውና ለኬብል ትራንስፖርት የሚያገለግሉ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎችን በሚያከናውነው የኩባንያው ይፋዊ አጋር የሚሰራ ይሆናል።

You might also like
Comments
Loading...