Fana: At a Speed of Life!

መቄዶንያ በባሕር ዳር ማዕከል ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል በባሕር ዳር ማዕከል ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ።

የማዕከሉ ክሊኒክ ኃላፊ እና የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ማኅተመ በቃሉ እንደተናገሩት፥ በባሕር ዳር ከተማ ከ2 ዓመታት በፊት ለድርጅቱ ግንባታ የሚውል 10 ሄክታር መሬት እንደተፈቀደላቸው አስታውሰዋል።

በቅርቡም ቦታውን በመረከብ ግንባታው እንደሚጀመር እና ግንባታው እስኪጠናቀቅ በተጓዳኝ ጊዜያዊ ማዕከል በማቋቋም በሦስት ወራት ውስጥ ለ300 ሰው አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

አቶ ማኅተመ ለግንባታ ሥራው ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተመደበ ጠቅሰው፥ በጀቱንም በበጎ ፈቃድ ድርጅቶች እና በተለያዩ ተቋማት እንደሚሸፈን ነው ያብራሩት።

ድርጅቱ በባሕር ዳር የሚገነባው የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን አስመልክቶ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል።

ህብረተሰቡም በ”8151″ ላይ “1” ቁጥርን ጽፎ መልዕክት በመላክ አንድ ብር ድጋፍ እንዲያደርግ በመርሀ ግብሩ ጥሪ ተላልፏል።

ድጋፍ የሚፈልጉ ግለሰቦችን በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ተቋም እና ማኅበረሰቡ ለድርጅቱ በሚሰጠው ጥቆማ እንደሚለዩም አቶ ማኅተመ አብራርተዋል።

ከስድስት ዓመታት በፊት 40 ግለሰቦችን በመያዝ በቢንያም በለጠ የተመሰረተው ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት እና ፆታ ሳይለይ ከ2 ሺህ በላይ አረጋውያንን ከወደቁበት በማንሳት እገዛ እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ማኅተመ አስታውቀዋል።

ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ድጋፉን በየአካባቢያቸው እንዲያገኙ ለማድረግም በሀረር፣ ሐዋሳ አሁን ደግሞ በባሕር ዳር ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ምንጭ፦አብመድ

You might also like
Comments
Loading...