Fana: At a Speed of Life!

860 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የለገዳዲ ቁጥር 2 የውሃ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 12፣2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 860 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገዉ የለገዳዲ ቁጥር 2 የውሃ ልማት ፕሮጀክት የግንባታ ስምምነት ተፈረመ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የውሃ አቅርቦት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ይታወቃል ።

የዚህ እንቅስቃሴ አካል የሆነው የለገዳዲ ቁጥር 2 የከርሰ ምድር ውሃ ልማት ፕሮጀክትን ለማስጀመር ግንባታውን ከሚያከናውኑ ስራ ተቋራጮች ጋር ስምምነት መፈረሙን የከንቲባ ፅህፈት ቤት አስታውቋል ።

ፕሮጀክቱ በሰሜንና ምስራቅ አዲስ አበባ የሚገኙ አከባቢዎችን በዋነኛነት በጉለሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ነው የተገለፀው።

እንዲሁም ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት አከባቢ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች እና ወረዳዎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በጀት የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሮጀክቱ በቀን 86 ሺህ ሜትር ኪዩብ የውሃ አቅርቦት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በዚህም 860 ሺህ የሚሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል።

በስምምነት ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ አዲሱ የከተማዋ አስተዳደር ሃላፊነቱን ሲረከብ 50 በመቶ የነበረው የውሃ አቅርቦት ሽፋን በርካታ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮን በማካሄድ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ 62 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይነትም ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ ሌሎች በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ እና ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ የከተማዋን የውሃ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በጋራ ተጠቃሚነት መርህም በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ከነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር እንደሚዘረጋ መግለፃቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like
Comments
Loading...