Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማሻሻያ አዋጅን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማሻሻያ አዋጅን አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባካሄደው 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ሁለት አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል፡፡

በጉባዔውም የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ በቀረበለት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ ነው የውሳኔ ሀሳቡን መርምሮ ያፀደቀው፡፡

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ሃላፊነት በማስፋት በግል ድርጅቶች የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎችን አቤቱታ በመቀበል ምርመራ ማካሄድ በማስፈለጉ የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ተብሏል፡፡

ከዚህ በፊት መርማሪዎች ሃላፊነት ተሰምቷቸው በድፍረት መመርመር እንዲችሉ ሲደረግ እንዳልነበር በውይይቱ ተገልጿል፡፡

በዚህም የተሻሻለው አዋጅ ላይ ልዩ መብት፣ የሰራተኞች ጥቅማጥቅም እንደተካተቱበትና በዋናነት አምስት ጉዳዮች እንዳሉትም ተጠቅሷል፡፡

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርበውን ሪፖርትና ውሳኔ እንዲሁም አስተያየት ተቀብሎ አስፈላጊውን እርማትና ማስተካከያ የማይወስዱ ተቋማት ላይ በቀጣይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እርምጃ የመውሰድ ሃላፊነት እንዳለበት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጉባኤው አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብን አስመልክቶ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በ2 ተቃውሞና በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.