Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የቻይና ዠዢንግ ግዛትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይናዋ ዠዢንግ ግዛትን በዛሬው እለት ጎብኝተዋል።

የዠዢንግ ግዛት ኮሚኒስት ፓርቲ ጸሐፊ ቼ ጁንም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድና ልዑካቸው በቻይና ምሥራቃዊ የጠረፍ ግዛት የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ወቅት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ባለሀብቶች አዲስ በተከፈቱ የኢንቨስትመንት መስኮች፣ በተለይም ወደ ግዛቲቱ የግብርና ውጤቶችን በማስገባት ላይ በበለጠ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዠዢንግ ግዛት ሀንዡ ከተማ ቆይታቸው የቻይናው አሊባባ ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችንም ጎብኝተዋል።

አሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ጃክ ማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አሊባባ ኩባንያን አስጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅትም ስለ ኩባንያው ማብራሪያ የሰጧቸው ሲሆን፥ ኩባንያው በዓለም ዙሪያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለ40 ሚሊየን ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ሀገራት በሩዋንዳ ብቻ ስራውን እየከወነ የሚገኘው ኩባንያው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ስራውን ለማስፋፋት እቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጉብኝቱ ወቅት፥ አሊባባ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨሰት እንዲያደረግ ግብዣ አቅርበዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስራ ፈላጊ ወጣት በመሆኑ አሊባባ ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርግ ውጤታማ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

አሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ጃክ ማ በበኩላቸው፥ በቀጣይ ዓመት ህዳር ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም ነው ያስታወቁት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቤጂንግ በሚካሄደው የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ነው ወደ ቻይና ያቀኑት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከጉባዔው በፊት ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬኪያንግን ጫምሮ ከሌሎች የቻይና ኩባንያዎች አመራሮች ጋር የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ እና ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

በሰላማዊት ካሳ

You might also like
Comments
Loading...