Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያና አማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአምቦ ከተማ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያና አማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአምቦ ከተማ ተካሄደ።
 
የህዝብ ለህዝብ መድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና ክልል አመራሮች እንዲሁም ከሁለቱ ክልሎች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
 
መድረኩ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ባልተገባ ትርክት ህዝብን ለማጋጨት የተወጠኑ ሴራዎችን በማክሸፍና ወንድምና እህት ህዝቦች በጋራ በመቆም ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
 
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በውይይት መድርኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰደቦችና ህዝቦች አንደነት ሰፊ መሰረት እንዳለው ተናግረዋል።
 
የኢትዮጵያ የአነድነት መሰረትም የህይወት መስዋትነት የተከፈለበትና በደም የተሳሳረ መሆኑንም አቶ ሽመልስ በንግግራቸው አንስተዋል።
 
ለዚህም የአድዋ፣ ካራማራና ሌሎች ድሎቸን በአብነት አንስተዋል።
 
የኦሮሞ ባህልና ማንነት አቃፊ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፥ በገዳ፣ በጉዲፈቻ፣ በሞጋሳና ሌሎች መንገዶች ሌሎችን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሱ አካል አድርጎ የሚኖር ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ባለፉት ጊዜያት የኦሮሞ ህዝብ ሌሎችን እንደሚያፈናቅልና እንደሚገፋ ሲሰቡኩ የቆዩ ትርክቶች ሲታዩ የነበረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
ይሁን እንጂ የኦሮሞ ህዝብ አባይን ተሻግሮ ከአማራ ህዝቦች ጋር ያለውን የወንድምና እህት አንድነት መሰረት በተግባር መሳየቱን አቶ ሽመልስ አስታውሰዋል።
 
በዚህም በሀገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ለታየው ለውጥ የራሱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ነው የተናገሩት።
 
የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህንን የአንድነት ሰፊ መሰረታቸውን ከመቼውም በላይ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
 
አባቶቻችን ኡለላዊት ኢትዮጵያን እንዳቆዩን እኛም ይህንን የአንድነት መሰረት በማጠናከር የበለጸገች ዴሞክራሲና ፍትህ የተረጋገጠባት አንደነቷ የማይነቀነቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንሰራለን ብለዋል።
 
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው፥ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል።
 
ይህም ሁለቱ ብሄሮች በሀገር ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ነው ያሉት ዶክተር አምባቸው፥ የኦሮሞና የአማራ አንድነት ሀገር ይገነባል፤ ከተለያዩ ግን ሀገር ያፈርሳል ሲሉም ተናግረዋል።
 
ሁለቱ ብሄሮች ጠላት በየጊዜው እየቀረፀ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በሚለቃቸው አጀንዳዎች ስሜት ውስጥ ሳይገቡ በተረጋጋ መንፈስ ነገሮችን በመመልከት ከመንግስታቸው ጎን ሊቆሙ ይጋል ሲሉም ገልፀዋል።
 
ከዚህ በኋላ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ያላቸው ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ የጠነከረ በመሆኑ በጋራ የማይፈቱት ችግር አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል።
 
በአማራ ክልል የኦሮሞ አስተዳደር ዞን ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘም ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ችግሩ የተከሰተው በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ አካላት በሸረቡት ሴራ ነው ብለዋል።
 
ሁለቱ ህዝቦች ከዚህ በኋላ በመደማመጥና ያላቸው በጋራ የመኖር እሴት በመጠቀም የጠላትን አጀንዳ መመከት እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።
 
የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በውይይት መድረኩ ላይ የመያያ መነሻ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
 
አቶ አዲሱ፥ በሀገራዊ ለውጡ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋቱን፣ የመናገርና የመጽሃፍ ነፃነቶች ተከብረው ከላይ ከተያያዙ ጎዳዮች ጋር በተያያዘ በእር ቤት የነበሩ ዜጎች መፈታታቸውን አስታውሰዋል፡፡
 
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ፍትህዊነትን ለማረጋገጥም እየተሰሩ ያሉ በርካታ ስራዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።
 
ይሁን እንጅ ለውጡ ተጋዳሮቶች እንዳሉበት የተናገሩት አቶ አዲሱ፥ የለውጡ ተቃራኒ ሃይሎች ከቻሉ ለውጡን በማደናቀፍ ከህግ የበላይነት ተጠያቂነት ለማምለጥ እንቅቃሴ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
 
በዚህም ወንድምና እህት ህዝቦችን በማጋጨትና የመከፋፋል እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
 
የዜጎች ሞት፣ አካል ጉዳትና መፈናቀል የለውጡ ተግዳሮቶች እንደሆኑ በመግለጽ፥ ህዝቦችን ከሚያስማሙ ይልቅ የሚያለያዩ ትርክቶች ላይ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።
 
ጽንፈኛ ብሄርተኛነትን በመታገል እና የሃሰት ትርክቶችን በማረም አሁን የተገኘውን ድል ወደ ኢኮኖሚ ድል ለመሸጋገር እንደሚገባም አመላክተዋል።
 
ለዚህም ዛሬ ከሚካሄደው መሰል ታላላቅ መድርኮች በተጨማሪ በአዋሳኝና ኩታ ገጠም ወረዳዎች የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን የባህልና ኪነ ጥበብ ማዕክላት ላይ ህዝብን ለህዝብ የሚያስተሳስሩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነቶቻቸውን የሚያርሙባቸው የሰላም እሴቶች ላይም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ነው በመነሻ ጽሁፋቸው ያቀረቡት።
You might also like
Comments
Loading...