Fana: At a Speed of Life!

የታይዋን ሃኪሞች ከአንድ ሴት አይን ቆብ ውስጥ በህይወት ያሉ ንቦችን አገኙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታይዋን ሃኪሞች ከአንድ ሴት አይን ቆብ ውስጥ በህይወት ያሉ ንቦችን ማግኘታቸውን አስታወቁ፡፡

አራት ንቦች የሴቷን እንባ በሚመገቡበት ወቅት በአይኗ ቆብ ውስጥ የተገኙ ሲሆን÷ ንቦቹ መሬት ውስጥ፣ ወይንም የዛፍ ጉሬ ውስጥ ማር የሚሰሩና በመጠንም አነስተኛ የሆነ ዝርያ ያላቸው መሆኑ ተነግሯል፡

በደብባዊ ታይዋን የምትኖረው የ20 ዓመቷ ወጣት የቤተሰቦቿን የመቃብር ቦታ በምታፀዳበት ወቅት አቧራ በአይኗ ገብቶባት እንደነበረ ተናገራለች፡፡

ወደ አይኗ የገባውን ባዕድ ነገር አሸዋ ወይንም አቧራ ሊሆን እንደሚችል ገምታ የነበራችው ወጣቷ በወቅቱ በራሷ መንገድ አይኗን ለማጽዳት እንደሞከረች ነው የተጠቆመው፡፡

ይሁን እንጅ እየቆየ የህመም ስሜቱ እየባሰባትና አይኗ ማንባቱን መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

በዚህም ወደ ፎዪን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የአይን ህክምና ክፍል ማቅናቷ ነው የተነገረው፡፡

የአይን ሃኪሞቹ ለወጣቷ ባደረጉት ህክምና ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አራት በህይወት ያሉ ንቦች ከአይኗ ቆብ ስር ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

የእነዚህ ንብ ዝርያዎች ከሰዎች ቆዳ ላይ በላብ መልክ የሚወጣውን ጨው የመቅሰም ባህሪ እንዳላቸው ቢታወቅም የሰዎች አይን ውስጥ በህይወት የመኖርና እንባ መመገባቸው ያልተለመደ ነው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡- odditycentral.com

You might also like
Comments
Loading...