Fana: At a Speed of Life!

በስልጤ ዞን ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በስልጤ ዞን ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ በሰዎች ህይወት ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ።

የጎርፍ አደጋው በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ እና በስልጤ ወረዳዎች በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ላይ መድረሱን የወረዳው አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ዩኒት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ትላንት ማሻውን በአካባቢው የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የሶስት ወንዞት የውኃ ሙላት የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉንም አስታውቋል።

በአደጋው ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከልም ሶስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፥ ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች ውስጥ የአራቱ አስክሬን መገኘቱንና የሁለቱን ለማግኘት ፍለጋው አሁን መቀጠሉም ተገልጿል።

በአደጋው እስካሁን በቁጥር ያልታወቁ የቤት እንስሳት በተለይም ከብቶች የሞቱ ሲሆን፥ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱም ተነግሯል።

የስልጤ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ  በበኩላቸው፥ በአደጋው ከ5 ሺህ 600 በላይ ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

342 ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል በውኃ መጥለቅለቁን የተናገሩት ኃላፊዋ 637 ቤቶችም በውኃ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ለተጎጂዎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለማድረግ ምግብና ምግ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ከክልል እና ከዞን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

መጪው ክረምት እንደመሆኑ መሰል አደጋዎች እንዳይደርሱ ከአሁኑ የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

በኤርሚያስ ቦጋለ

You might also like
Comments
Loading...