Fana: At a Speed of Life!

የእሳት አደጋ አውሮፕላኗ ከደባርቅ ውሃ በማመላለስ በሰሜን ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን እሳት እያጠፋች ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእሳት አደጋ አውሮፕላኗ ከደባርቅ ውሃ በማመላለስ በሰሜን ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን እሳት እያጠፋች ነው፡፡

በዛሬው ዕለት ወደ ጎንደር ያቀናችው ሄሊኮፕተር  ደባርቅ አካባቢ ውሃ የመያዝና የመርጨት ሙከራዋን ካደረግች በኋላ ነው ወደ በሰሜን ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን እሳት ማጥፋት የጀመረቸው፡፡

በፓርኩ አካባቢ ያሉ የውሃ አማራጮችን ለመጠቀም ከፓርኩ ሰራተኞች ጋር ግንኙነት ከተደረገ በኋላ ሂሊኮፕተሯ ወደ እሳት አደጋ ቦታው እንደተሰማራች የአማራ ክልል ደንና ዱር እንሰሳት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ለዚሁ ተግባር ከኬንያ ዛሬ ጠዋት የገባችው ይህችው ሄሊኮፕተር ከ1ሺህ እስከ 1ሺህ 200 ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም አላት ተብሏል፡፡

እንዲሁም በፓርኩ የተከሰተውን እሳት ለማጥፋት ድጋፍ የሚያደርጉ 12 አባላት ያሉት የእስራኤል የሰደድ እሳት አደጋ ሙያተኞች ቡድን ዛሬ ጠዋት ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ኦር ዳንኤሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እስራኤል የኢትዮጵያ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው የባለሙያዎች ቡድኑን የላከቸው።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ባለፈው አርብ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከእስራኤል አቻቸቸው ብኒያሚን ንታኒያ ጋር በእስራኤል ድጋፍ ዙሪያ በስልክ መወያየታቸውንም ነው ያመለከቱት።

12 አባላት ያሉት ይህ የባለሙያዎች ቡድን ከእስራኤል የእሳት አደጋ ብርጌድ የተውጣጣ ሲሆን፥ በሰደድ እሳት ከፍተኛ እውቀት እና ሙያ ያላቸው መሆናቸውን ምክትል አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሣውን እሳት ለማጥፋት የእሳት አደጋ ሄሊኮፕተሮችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ትናንት ማምሻውን መግለፁ ይታወሳል።

You might also like
Comments
Loading...