Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከባለሃብቶች የተነጠቁ ቦታዎች አሁንም ያለ አገልግሎት መቀመጣቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል  

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 14 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለረጅም ጊዜ ያለ ስራ ታጥረው በመቀመጣቸው ከባለሃብቶች የተነጠቁ ቦታዎች አሁንም ያለ አገልግሎት መቀመጣቸውን የመዲናዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ለባለሃብቶች ተሰጥተው ያለስራ ለበርካታ አመታት ታጥረው የተቀመጡ ሰፋፊ መሬቶችን የከተማ አስተዳደሩ በወሰደው እርምጃ ወደ መሬት ባንክ ማስገባቱ የሚታወስ ነው።

አስተዳደሩ አጥረው ካላለሙ ባለሃብቶች ወደ መሬት ባንክ ያስገባቸውን ባዶ ቦታዎች በድጋሚ ጥቅም ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሲገልጽ ቆይቷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የተወሰኑትን ለአረጓዴ ልማት ፕሮጀክት ያዘጋጀ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ የከተማዋን ወጣቶች በማደራጀት በጊዜያዊነት ለመኪና ማቆሚያ (የፓርኪንግ) አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ መቻሉ ይጠቀሳል።

በዚህ መልኩ አንዳንድ ስራዎች ቢሰሩም አሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ ቦታዎች የከተማዋን ገጽታ በማበላሸት ለቆሻሻ ማከማቻነት እየዋሉ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ያነሳሉ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በካዛንችስ፣ ፒያሳ እና አራት ኪሎ ባደረገው ቅኝት የተወሰኑ ቦታዎች ለአረንጓዴ ልማት እና ለመኪና ማቆሚያነት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን መታዘብ ችሏል።

ይሁን እንጅ ከዚህ በተቃራኒው የቆሻሻ መጣያና መጸዳጃ የሆኑ ስፍራዎች መኖራቸውንም ለመታዘብ ችለናል።

አስተያየት ሰጭዎችም መሬቶቹ ወደ ከተማ አስተዳደሩ መመለሳቸው ተገቢ ቢሆንም ወደ ታለመላቸው አላማ በጊዜ አለመግባታቸውና አጥራቸው መፍረሱ ይበልጥ ለቆሻሻ ማከማቻ ምቹ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በነዋሪው ጤና ላይ የጤና እክል በማስከተል የደህንነት ስጋት መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አለሙ መሬቶቹ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ጊዜያዊ እና ዘላቂ ፕሮጄክቶችን በመንደፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም ክፍት ቦታዎችን ለአልሚዎች በመስጠት ሂደት መሰል ችግሮች እንዳያጋጥሙ ይሰራልም ነው ያሉት።

አስተዳደሩ ከአልሚዎች የተቀሙ ክፍት ቦታዎች ወደ ልማት እንዲገቡ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጿል።

 

 

በሲሳይ ጌትነት

 

You might also like
Comments
Loading...