Fana: At a Speed of Life!

ሳዑዲ አረቢያ የአሜሪካዊው የአማዞን ኩባንያ ባለቤትን ስልክ ጠልፋለች ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳዑዲአረቢያ የአሜሪካዊው የአማዞን ኩባንያ ባለቤትን ስልክ ጠልፋለች ተባለ።

ሳዑዲ የአማዞን ኩባንያ ባለቤት ጄፍ ቤዞስን ስልክ ከመጥለፍ ባሻገር መረጃችንም ስለማግኘቷ መርማሪው ጌቪን ዲ ቤከር አስታውቋል።

ጄፍ ቤዞስ የዋሽንግተን ፖስት ባለቤት መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ ባለፈው ጥቅምት ወር በቱርክ የሳዑዲ ኤምባሲ ውስጥ የተገደለው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂም በዚያ ይሰራ ነበር።

ግድያውን ተከትሎ ታዲያ የቤዞሱ ዋሽንግተን ፖስት ተከታታይነት ያላቸውና ሰፊ መረጃዎችን ስለጋዜጠኛው አሟሟት ሐተታዎችን እያወጣ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ከጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ጉዳይ ጋር በተያያዘም ሳዑዲ ከቤዞስ ጋር በጠላትነት መተያየት መጀመሯ ተነግሯል።

ሆኖም ሳዑዲ አረቢያ እስከአሁን ድረስ እየቀረበባት ያለውን ክስ አስመልክቶ የሰጠችው አስተያየት የለም ተብሏል።

ባለፈው ጥቅምት የተካሄደውን ግድያ ተከትሎ ከዚህ ቀደም ከሳዑዲ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የሚጠረጠርና ጭምጭምታዎችን በማውጣት የሚታወቀው አንድ ታብሎይድ የቤዞስን የግል መረጃ በገጹ ላይ ይዞ መውጣቱ ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ታዲያ ቤዞስ ስልኩ እንዴት ሊጠለፍ እንደቻለ የግል መርማሪዎችን በመቅጠር  ውጤቱን ሲጠባበቅ እንደነበር ተሰምቷል።

በቱርክ የሚገኘውን የሳዑዲ ኤምባሲን በመጥለፍ ስሙ የሚነሳው የግል መርማሪው ጌቪን ዲ ቤከርም ከባለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ የሳዑዲ መንግስት ጄፍ ቤዞስ ላይ ችግር ለመፍጠር እየሞከረ እንደነበር ገልጿል።

በዋሽንግተን የሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲም ስለጉዳዩ ተጠይቆ እስከአሁን ምላሽ ያለመስጠቱን መርማሪዎቹ አስታውቀዋል።

 

ምንጭ፦ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like
Comments
Loading...