Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከዓለም አቀፉ ህፃናት አድን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ካሮልይን ሚለስ ጋር ተወያዩ።

ፕሬዚዳንቷ ድርጅቱ በኢትዮጵያ አጋርነቱን ማጠናከር ባለበት ወቅት የሚጠበቅበትን ሚና መወጣቱን ለዋና ስራ አስኪያጇ ገልጸውላቸዋል።

የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች አተገባበርና ስልቶች ላይም ውይይት ማድረጋቸውን ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ካሮልይን ሚለስ በበኩላቸው ድርጅቱ ትኩረት በሚያደርግባቸው ትምህርት፣ የህፃናት ጤና አጠባበቅና የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አብራርተዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለውጦች እየታዩ መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጇ ድርጅቱ ወደ ፊት ለኢትዮጵያ የሚኖረውን አጋርነት አረጋግጠዋል፡፡

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ13 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር በመስራት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 10 ሚሊየን ያህል ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ዋና ስራ አስኪያጇ አንስተዋል፡፡

በተያያዘ ኤና ፕሬዚዳንቷ ማሪዮት ኢንተርናሸናል በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተባብሮ መስራት በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አርን ሶርሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው በኢትዮጵያ የቱሪዝም በተለይም ደግሞ የመስተንግዶው ዘርፍ በፍጥነት እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች እንደሉ መግለጹን ከፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ ሂደት ደግሞ ማሪዮት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው የኩባንያውን ተነሳሽነት በማድነቅ የፕሮጀክት ሃሳቦቹ እንዲሳኩ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

You might also like
Comments
Loading...