Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎበኙ።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ ለሚኖራቸው የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት ላሊበላ ከተማ ከገቡ በኋላ ነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን የጎበኙት።

መሪዎቹ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኘውን ቤተ ጊዮርጊን በጋራ በመሆን ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ ፕሬዚዳንት ማክሮን ባዩት ነገር መደመማቸውን እና ለቅርሱ ጥገና ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንዳረጋገጡላቸው አስታውቀዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፥ ባዩት ነገር መደመማቸውን ተናግረዋል።

ቅርሶቹን በአካል ተገኝተው መመልከታቸው ቅርሱን ለመጠገን እና ለመጠበቅ ለሚደረገው ድጋፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር እብይ አህመድ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በፓሪስ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ፈረንሳይ ለላሊበላ ቅርስ ጥገና ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀው ነበር።

ፈረንሳይም ለቀርሱ ጥገና ድጋፍ እንድታደርግ ማረጋገጧን ተከትሎ ነው የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዛሬው እለት ቅርሶቹን በአካል ተገኝተው የጎበኙት።

በአልአዛር ታደለ

You might also like
Comments
Loading...